ባንኩ ከወለድ-ነጻ የብድር አገልግሎት ለመሰጠት እያደረገ ያለው ዝግጅት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ ከወለድ-ነጻ የብድር አገልግሎት ለመሰጠት እያደረገ ያለው ዝግጅት አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው
ሰመራ፣ ግንቦት 22/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከወለድ-ነጻ የብድር አገልግሎት ለመሰጠት እያደረገ ያለው ዝግጅት አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የተፈጥሮ ሃብቱን አልምቶ እራሱንና ሀገሩን እንዲያሳድግ እድል የሚፈጥር መሆኑ ተገለጸ።
ባንኩ በክልሉ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ያዘጋጀው ስልጠና ዛሬ በሰመራ ከተማ ተጀምሯል።
የአፋር ክልል ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አሊ ሁሴን እንዳሉት ክልሉ በርካታ የተፈጥሮ ሃብቶችና ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሉበት አካባቢ ነው።
በክልሉ በሆቴልና ቱሪዝም ፣ በማዕድን ልማት፣የእንስሳት እርባታና እርሻ ልማት ሰፊ አማራጮች መኖራቸው ለአነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችም ሆነ ለኢንቨሰተሮች ምቹ ሁኔታ ነው ብለዋል።
አሁን ላይ የስራ ፈጠራ ባህሎች አየተሻሻሉ በመምጣታቸውና የባንኮች የብድር አቅርቦት በመመቻቸቱ ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የአካባቢውን ህብረተሰቡን እምነትና ባህል መሰረት በማድረግ ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት ለማቅረብ የጀመረው ጥረት የአርብቶ አደሩን ህብረተሰቡ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት ከራሱ አልፎ ሀገሩን እንዲጠቅም የሚያስችል ነው ብለዋል ።
ኢንተርፕራይዞቹ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል የተፈጠረላቸውን እድል እንዲጠቀሙበት አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የደሴ ዲስትሪክት ሃላፊ አቶ ፉአድ መሀመድ በበኩላቸው
ሀገራዊ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን በመደገፍ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካትና ሰፊ የስራ እድል በሚፈጥሩ መስኮች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል።
በዘርፎቹ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው አንቀሳቃሾች በቢዝነስ እቅድ አዘገጃጀት፣ በሂሳብ አስተዳደር፣ ንግድ ስራ አመራርና በገበያ ፍለጋ አስተዳደር ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ባንኩ የህብረተሰቡን እምነትና ባህል መሠረት ያደረገ ከወለድ ነጻ ብደር አገልግሎት በክልሉ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ በቀረበው እድል ተጠቃሚ እንዲሆን የክልሉ መንግስት የመስሪያ ቦታና መሠረተ ልማቶችን በማሟላት ከሊዝ መሬት አዋጅ ጋር ያሉ ማነቆዎችን መፍታት ይጠበቅበታል ብለዋል።