በጎንደር የጃኖ የባህል ልብስ ገበያ ደርቷል

ጎንደር ጳግሜ 4/2010 በጎንደር አካባቢ በስፋት እየተዘወተረ የመጣው ጃኖ የባህል ልብስ በዘመን መለወጫ በአል የገበያ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን የጎንደር ከተማ ነጋዴዎችና ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡ ጃኖ በቀደምት የጎንደር ነገስታት ዘመን በስፋት እንደሚለበስና የጀግንነትና የመሰዋእትነት ተምሳሌት በመሆን በትውልድ ቅብብሎሽ አሁን ላይ መድረሱን የከተማው ባህል ማእከል አስታውቋል። ወይዘሮ መልሺው አስማረ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በአሉን ምክንያት በማድረግ ለ12 አመት ወንድ ልጃቸው የተሰፋ ጃኖ ለመግዛት ጥበብ ተራ መምጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ "የጃኖ ልብስን ታሪካዊ ዳራ በሚገባ ባላውቀውም አሁን ላይ ወጣቱም አዛውንቱም ሆነ ሴቶች ጭምር በጃኖ ልብስ አዲሱን አመት ደምቀው ለመታየት እየገዙ ነው" ያሉት ወይዘሮዋ ለልጃቸው በማራኪ ዲዛይን የተሰራ ልብስ በ500 ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል። "የጃኖ ልብስ በጎንደርና አካባቢው በሁሉም የእድሜ ደረጃ በስፋት እየተዘወተረ መጥቷል" የምትለው ደግሞ ወይዘሪት አይናለም አበራ የተባለችው የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናት፡፡ በዘንድሮ የዘመን መለወጫ በአል ጥለቱ በቀይ የሀር ክር የተዋበውንና በመስቀል ቅርጽ የተጠለፈውን የሴቶች ጃኖ ልብስ በ1ሺ 600 ብር መግዛቱዋን ተናግራለች፡፡ ቅዳሜ ገበያ ውስጥ የጥበብ ልብሶችን በመሸጥ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ሀዋ መሀመድ "በተለይ በቀይ ጥለት የሚዘጋጀው የሴቶች የጃኖ ልብስ በዘንድሮ የዘመን መለወጫ ተፈላጊነቱ ጨምሯል" ብለዋል፡፡ ለአዋቂ ሴቶች በጃኖ ጥለት የተሰራ የሴቶች ጥበብ ከፍተኛው 1ሺ 800 ብር ዝቅተኛው ደግሞ 1ሺ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጸው የሴት ህጻናት ደግሞ 700 ብር እንደሚያወጣ ገልጸዋል። አቶ አብደላ ኑርሁሴን የተባሉ የሀገር ባህል አልባሳት ነጋዴ ደግሞ "በአዲሱ አመት የጃኖ አልባሳት ገበያ የደራ ሆኖአል" ብለዋል፡፡ በሱቃቸው ውስጥ ለአዋቂ ወንዶችና ለህጻናት የሚሆኑ የጃኖ አልባሳት ለሽያጭ ማቅረባቸውን ተናግረው ለአዋቂ ወንዶች 1ሺ 400 ብር ለወንድ ህጻናቶች ደግሞ 500 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። የጃኖ አልባሳት በማንኛውም የእድሜ ክልል ለሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ማራኪ በሆኑና የዘመኑን ፋሽንና ባህል በተከተለ መንገድ ዲዛይን ተደርገው በመሰፋታቸው የገበያ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ባህል ማእከል ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ስለሺ መስፍን በበኩላቸው ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የጃኖ አልባሳት በህብረተሰቡ ዘንድ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡ “በመጻህፍት ተጽፎ የተገኘ የታሪክ ማስረጃ ባይኖርም በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት የጃኖ ልብስ በመኳንንቱና በመሳፍንቱ እንዲሁም በወይዛዝርት ጭምር ይዘወተር ነበር” ብለዋል፡፡ የጃኖ ልብስ በቀይ ጥለት ያሸበረቀ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያዊን የጀግንነት መገለጫ አመልካች ባህላዊ ልብስ መሆኑንም ሃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል፡፡                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም