አይርላንድ በኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ትደግፋለች--አምባሳደር ኒኮላ ብረናን

103

ግንቦት 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) አይርላንድ በኢትዮጵያ የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብረናን ተናገሩ፡፡

በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱም በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብረናን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩም በተለይ አፋርና ሶማሌ ክልሎች የሴት ልጅ ግርዛትና ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የሚከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ኒኮላ ብረናን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አየርላንድ በኢትዮጵያ የሥርዓተ- ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራትን ስትደግፍ መቆየቷን አስታውሰዋል፡፡

አገራቸው በቀጣይም ይህንኑ ተግባር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአይርላንድ መንግሥት በተለይ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት የሚከናወኑ ተግባራትን እንደምትደግፍ ጠቅሰው፤  ለዚሁ ሥራ የሚውል የስድስት ዓመት መርሃ-ግብር መዘጋጀቱንም አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሥርዓተ-ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት በስፋት መከናወን እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም