በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በመጪው ክረምት የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል
አዲስ አበባ ግንቦት 22/9/2014 /ኢዜአ/ በመጪው የክረምት ወቅት ጎርፍና መሰል አደጋዎች ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ስለሚኖር የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ።
ሰሞኑን የታየው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ክስተቶች የመጣ መሆኑ ተጠቁሟል።
በኢንስቲትዩት የአየር ሁኔታና የአየር ጠባይ ትንበያ ባለሙያው ታምሩ ከበደ እንደገለጹት፤ በቀጣዩ ክረምት ወቅት ከመደበኛው በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች ያመለክታል።
የላሊና የአየር ጠባይ ለውጥ ሳቢያ በአገሪቱ በበልግም ሆነ በመኸር ወቅቶች ደረቅ ወራት በዝተው መስተዋላቸውን የገለጹት ባለሙያው ከዚህ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ሓምሌና ነሀሴ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
በተለይም በአገሪቱ በሰሜን ምስራቅና በምስራቅ አካባቢዎች ላይ ዝናቡ እየጨመረ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።
ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው ከፍተኛ የሙቀት መጠን የላሊኖ ተፅእኖ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ጋር ተያያዥ መሆኑን ለጎርፍ አደጋ ሥጋት እንደሚሆነም አብራርተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፤ የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ከወዲሁ አደጋዎች እንዳይፈጠር ኅብረተሰቡም ሆነ ተቋማት ከወዲሁ የመከላከል ሥራ ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል።
በተለይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ፣ በወንዞችና ተዳፋትማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተጠናከረ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በአገሪቱ የተከሰተው ላሊና የመኸርና በልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑትን የቦረና፣ ባሌ ሶማሌና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎች በቂ ዝናብ እንዳያገኙ ምክንት መሆኑንም አስታውሰዋል።
የአደጋ ሥጋትና አመራር፣ ጤና ሚኒስትር፣ ግብርናና ሌሎች መሰል የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላሊኖ የሚፈጥረውን አደጋ ለመመከት ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ከግንቦት ወር መጀመሪያ ጀምሮ የሙቀቱ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው በከተሞች መስፋፋትና የውኃ አካላት መመናመን ምክንያት መሆኑንም ነው ያነሱት።
ኅብረተሰቡም የተለያዩ ተክሎችን በመትከልና በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥን የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖዎች መቋቋም እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።