ኤጀንሲው ካዘጋጀው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር 27 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው ካዘጋጀው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር 27 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል
አዲስ አበባ ግንቦት 22/9/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ኅበረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት ባካሄደው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር 27 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ዓሊ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን፣ በዛርና ሲምፖዚየም የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የተለያዩ ተቋማት እንዲሳተፉ መደረጉን ገልፀዋል።
በበዛሩም ከአዲስ አበባና ከስድስት ክልሎች በተለያዩ የኅብረት ሥራ ዘርፎችና ከኅብረት ሥራ ሴክትር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ተቋማት መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የተለያዩ ምርቶችን በማስተዋወቅ የግብርና የኢንዱስትሪ ምርቶችና የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሽያጭ ማቅረባቸውንም ነው የጠቆሙት።
በዚህም በከተማዋን የገበያ ዋጋ ማረጋጋት ተችሏል ብለዋል።
ኤጀንሲውም እንደ ኅብረት ሥራ ማኅበርም ካዘጋጀው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛር 27 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ በበኩላቸው የዋጋ ንረት በማረጋጋት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው ብለዋል።
በመዲናዋም የተከናወነው የመጀመሪያው ከተማ አቀፍ ኤግዚቢሽን፣ በዛርና ሲምፖዚየም የኅብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ድርሻን ለማሳደግና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦ ያደርጋል ነው ያሉት።
የመጀመሪያው ከተማ አቀፍ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ከግንቦት 18 እስከ 21 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ከ22 በላይ የሚሆኑ አምራቾች መሳተፋቸው ይታወሳል።