በአማራ ክልል ካሉ ሁለት የብረታ ብረት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱን የትራክተር መገጣጠሚያ ለማድረግ እየተሰራ ነው

75

ባህር ዳር፤ ግንቦት 21/2014 (ኢዜአ)፡ ..በአማራ ክልል የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ካሉ ሁለት የብረታ ብረት ፋብሪካዎች ውስጥ አንዱን የትራክተር መገጣጠሚያ እንዲሆን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።

የአማራ ክልል  መንግስት በዛሬው ዕለት 136 የእርሻ ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች አስረክቧል።

ዶክተር ይልቃል ከፋለ በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የግብርና ቴክኖሎጂ መጠቀም ወሳኝ ነው።

የክልሉ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ  ለማሳደግና ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤  አርሶ አደሩ መስኖን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና አማራጮችን በመጠቀም ማምረት እንዲችል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ወጣቶችን በማደረጃትና የትራክተር ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ለአርሶ አደሩ በኪራይ እንዲያርሱ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ይህም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

''ሁል ጊዜ ቴክኖሎጅን ከውጭ በማስመጣት የአርሶ አደሩን ፍላጎት ማርካት አይቻልም'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ የዘር ግብዓት ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ትራክተርና ሌሎች የመስሪያ ማሽኖችን በራስ አቅም መስራት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ ቴክኖሎጅን ለመጠቀም እያሳየ ያለው ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው መንግስትም  የአርሶ አደሮን ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግስት ካሉ ሁለት የብረታ ብረት ፋብሪካዎች  አንዱን የትራክተር መገጣጠሚያ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል አክለውም በሚቀጥለው ዓመት ለትራክተር፣ ለኮምፓይነር እና ለውሃ መሳቢያ ሞተር መግዣ የሚሆን  1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መፈቀዱን አስታውቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው "ቴክኖሎጅ  ለማቅረብና  ለቴክኖሎጂ መጠቀም  ስራ ቅርብ ሁነን ትልልቅ ውሳኔዎችን መወሰን አለብን" ብለዋል።

ቴክኖሎጅን ከማቅረብና  ከመጠቀም አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቆመው፤ አሁን ላይ እንደ ክልል ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ማምረት ካልተቻለ ከድህነት መላቀቅ አይቻልም ያሉት  አቶ ግርማ፤ ለዚህ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

በአማራ ክልል ለ2014/2015 የመኸር ሰብል  ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማሪያም ከፍያለው ናቸው።

የምርት መጠኑንም በሄክታር  ከ24 ነጥብ 5 ኩንታል ወደ 29 ነጥብ 5 ኩንታል ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል  ለእርሻ ምቹ ከሆነው መሬት ውስጥ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በትራክተር ለማረስ አመች መሆኑን ገልጸው፤  ነገር ግን በትራክተር እየታረሰ ያለው ከ20 በመቶ ያልበለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ከ800 ያልበለጡ ትራክተሮች መኖራቸውን ገልጸው፤ በዚህ ዓመት መንግስት በወሰደው ቁርጠኛ አቋም ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።

መንግስት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታና መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው ያሉት ደግሞ ትራክተር ከተረከቡ አርሶ አደሮች መካከል የምእራብ ጎጃም ዞን ወንበርማ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት  አርሶ አደር ይበልጣል አዳሙ ናቸው።

በትራክተር መጠቀም ጉልበትና ጊዜን ካላስፈላጊ ብክነት ከመታደግ ባለፈ የምርት መጠንና ጥራትን ለማሳደግም ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም