በመዲናዋ የደንብ ጥሰቶችን በተሻለ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የደንብ ጥሰቶችን በተሻለ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ ነው
ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአዲስ አበባ የደንብ ጥሰቶችን በተሻለ መልኩ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ አዲስ ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አስታወቀ።
በከተማ አስተዳደሩ የደንብ መተላለፍ በዓይነትና በቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አዲስ የቁጥጥር ስልት ተግባራዊ ማድረግ ማስፈለጉ ታውቋል።
ለደንብ ማስከበር በችግርነት ከሚነሱት መካከል የህዝቡ ተሳትፎ ማነስ፣ የአንዳንድ ደንብ ተቆጣጣሪዎች የግንዛቤ ማነስና የስነ ምግባር መጓደል እንዲሁም የአንዳንድ አስፈፃሚ አካላት ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳሉ።
የደንብ ጥሰት ሲያጋጥም በጊዚያዊነት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የችግሮቹ ምንጭ ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት አለመስራት ሌላው ችግር መሆኑ ተገልጿል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ፉፋ፤ የደንብ መተላለፍ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት አዲስ የአሰራር ስርአት መዘርጋት ማስፈለጉን ይናገራሉ።
በሰው ኃይል እስከ ታችኛው እርከን በባለስልጣኑ አዲስ አደረጃጀት ተሰርቶ መጠናቀቁን ጠቁመው ይህም የደንብ መተላለፎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያግዛል ብለዋል።
ባለስልጣኑ የሚመራበት ደንብ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለፍትህ ቢሮ መላኩን ጠቁመው ደንቡን ተከትሎ መመሪያ የሚዘጋጅ ስለመሆኑን ተናግረዋል።
የደንብ ማስከበር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመሆን ጥናት በመካሄድ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአዲስ መልክ የተዘጋጀው ደንብ ከዚህ በፊት የነበሩ የአሰራር ጉድለቶችን መነሻ ያደረገ መሆኑንም አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል።
የመሬት ወረራ፣ ህገ ወጥ ግንባታ፣የጎዳና ላይ ንግድን ጨምሮ ሌሎችንም ለመከላከልና ለመቆጣጠር የደንቡ መዘጋጀት ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል።
የደንብ መተላለፍን በመከላከል ሂደት በተለይም የአንዳንድ አስፈፃሚ ግለሰቦች ጣልቃ ገብነት እንቅፋት እንደነበር አስታውሰው በቀጣይ ማቆሚያ ሊበጅለት ይገባል ብለዋል።
የኮንትሮባንድ ንግድ መበራከትና የዘርፉ ተዋናዮች መበራከትም የደንብ ማስከበር እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ተብሏል።