የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የማጣራት አቅሙን በማሳደግ በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያጣራ እንደሚገኝ ተገለጸ

162

ግንቦት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የውሃ ማጣራት አቅሙን በማሳደግ በቀን 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።

የብዙ ተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ "የውሃ ማማ" እየተባለ ቢነገርላትም ጥቅም ላይ በማዋል በኩል ግን ብዙም ሳይሳካላት ቆይቷል።

በተለይም በከተሞች መስፋፋት ሳቢያ የነዋሪው እና የውሃ አቅርቦቱ መመጣጠን ባለመቻሉ እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውሃ አመራረት ውስብስብነት ታክሎበት የውሃ እጥረት ሲያጋጥም ይስተዋላል።

በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ኬዝ ማናጀር ሚስባህ ኤልያስ፤ የቃሊቲ ፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ የውሃ ማጣራት አቅሙን በማሳደግ በቀን እስከ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ በማጣራት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በቀን 7 ሺህ 500 ሜትር ኪዩብ ውሃ የነበረው የማጣራት አቅሙ አሁን ላይ የማጣራት አቅሙ 100 ሺህ ሜትር ኪዩብ መድረሱን ተናግረዋል።

የገጸ ምድር ለገዳዲና ድሬ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ ተክሌ ቱፋ፤ ጣቢያው ውሃ ለማምረት እና ለማከም የሚያግዙ ኬሚካሎችን የማምረት ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በቀን ከ195 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሀ የማምረት አቅም ላይ መድረሱን ጠቁመው ውሃን አክሞ ለማሰራጨት የሚወጣውን ገንዘብ እና ጉልበት በመረዳት ማህበረሰቡ ብክነትን በማያስከትል መልኩ ሊጠቀም ይገባል ብለዋል።

በውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን የከርሰ ምድር ውሀ ምርት ኬዝ ማናጀር ጋሻው መንግስቴ፤ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግር በውሃ በአቅርቦቱ ላይ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በአቃቂ የከርሰ ምድር ውሀ ማመንጫ 170 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሀ ታክሞ እየተመረተ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቅሰው ከመልከአ ምድራዊ አቀማመጥ አንጻርም ወደ ሚፈለግበት ቦታ ለማድረስ ከፍተኛ ሀይል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም