ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ በተደራጀ መልኩ እንዲካተት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

49

ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት በመደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ በተደራጀ መልኩ እንዲካተቱ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ያዘጋጀው  ሁለተኛው አገር አቀፍ  የሁለተኛ ደረጃ  ምስለ-ችሎት ውድድር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እንደጠቆሙት፤ በሀገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን  የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመቀነስ ከታችኛው ክፍል ጀምሮ  ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሊከናወነ ይገባል፡፡

በመሆኑም ኮሚሽኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የሰብዓዊ መብቶች ትምህርት እንደ አንድ መደበኛ የትምህርት አይነት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ  እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ  ኮሚሽኑ አዲስ  ስትራቴጂ ነድፎ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ሰፊ ሥራ እያከናወነ  መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛረ የተካሄደው ሁለተኛው ዙር የምሰለ-ችሎት ውድድር የዚሁ ስራ አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በውድድሩ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢ የመጡ 63 ትምህርት ቤቶች ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 130 ተማሪዎች በውድድሩ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ተሳታፊዎቹ ውድድሩን ከመካፈል ባሻገር ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ውድድሩ ስለሰብዓዊ መብት በቂ ግንዛቤ ያላቸውና ለነገ ራእይ የሰነቁ ወጣቶችን በማፍራት ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

የውድድሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ውድድሩ ስለሰብዓዊ መብቶች ያላቸውን ግንዛቤ እንዳሻሻለላቸው ተናግረዋል፡፡

ከአማራ ክልል አዘዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ እንድሪያስ አድማሱ፤ በውድድሩ የሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት የተሻለ ግንዛቤ ማግኘቱን ጠቁሞ፤ በቀጣይ የሰብዓዊ መብቶችን የሚያከብር ትውልድ መፍጠር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት ተናግሯል፡፡

የሰባዊ መብቶች መከበር ለሰላም መሰረት መሆኑንም ነው የገለጸው፡፡

ከሐረር ማሩፍ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ማክዳ ዘውዴ በበኩሏ፤ ሰብዓዊ መብቶችን በሚመለከት ከቤተሰብ ጀምሮ  ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ተናግራለች፡፡

ይህም የሌሎችን መብት አክብሮ የራሱን መብት ለማስከበር የሚሰራ ትውልድ ለመፍጠር ያግዛል ነው ያለችው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም