ህዝቡ ውስጥ የተሰገሰጉ የብሄር፣ የፖለቲካና የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር እሴትን አደጋ ላይ ጥለዋል

ደብረብርሀን፣ ግንቦት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ህዝቡ ውስጥ የተሰገሰጉ የብሄር፣ የፖለቲካና የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር እሴትን አደጋ ላይ መጣላቸውን የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ገለፁ።

በአማራ ክልል ከሰሜን ሸዋ እና ከኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የፀጥታ አካላት የተሳተፉበት የሰላም ውይይት መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሂዷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ህዝቡ ውስጥ የተሰገሰጉ የብሄር፣ የፖለቲካና የጦር መሳሪያ ነጋዴዎች ተባብሮና ተከባብሮ የመኖር እሴትን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ተባብሮና ተከባብሮ መኖርን አደጋ ላይ የጣሉ ሃይሎች በወንድማማቾች መካከል ጥላቻ በመዝራት የህይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደምና የዜጎችን ከቀዬአቸው መፈናቀልን ማስከተላቸውን ገልጸዋል።

ካለፈው ትምህርት በመውሰድ የህዝቦች አብሮ የመኖር እሴት ጎልብቶ ዜጎች ከቦታ ቦታ በነፃነት ተቀሳቅሰው ሃብት ፈጥረው መኖር እንዲችሉ መንግስት የጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አጥፊዎችን በመለየት እርምጃው መወሰድ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በሂደቱ ንፁሀን ሰለባ እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ጥላቻ እያሰራጩ ያሉ ሚዲያዎች ከድርጊታቸው ተቆጥበው ለህዝባቸውና ሃገራቸው ሲሉ ሚዛናዊና ትክክለኛነት መረጃ በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መክረዋል።

ቂም በቀልና ጥላቻ ተወግዶ የሰላም እሴቶች ጎልብተው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ህብረተሰቡን በማስተማር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የኦሮሞ እና የአማራ ህዝብ ከትውልድ ትውልድ የተሻገረ የጋራ ታሪክና እሴት ያለው ህዝብ መሆኑን የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ የአሸባሪ ሃይሎችን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ማክሸፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በህብረተሰቡ መካከል ፀንቶ የቆየውን የሰላምና የአንድነት እሴቶችን በመሸርሸር ግጭት እንዲፈጠርና ሰላም እንዲታጣ ለሚያደርጉ ሃይሎች በር መክፈት እንደማይገባ አስረድተዋል።

የአጥፊ ሀይሎችን እኩይ ሴራ ተቀናጅቶ በዘላቂነት በማክሸፍ የሁለቱ ህዝቦች የቀደመ ቤተሰባዊ አኗኗሯቸው እንዲቀጥል የተጀመረው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሰራለን ብለዋል።

ሰላምና አንድነት ተቀራርቦና በሰከነ መንገድ ከልብ ተነጋግሮ ችግሮችን በመፍታት የሚመጣ በመሆኑ ይህ እንዲሆን እንሰራለን ሲሉ ገልፀዋል።

ያለፈውን በደል በመርሳትና በመተው መጪው ጊዜ የፀና ሰላም እንዲሆን የሰላም እሴቶችን በማጎልበት በቀናነትና በመተባበር መንፈስ እንሰራለን ብለዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ እንግዳው ጠገናው በእንዳሉት በኩላቸው ግጭት ጠማቂዎች ሁለቱ ወንድማማች ህዝብ መካከል መልካም ግንኙነት እንዳይኖር የሚችሉትን ሁሉ ሰርተዋል።

የግጭቱ ሴራ የተደረሰበት በመሆኑ በአካባቢው እንደ ቀደመው ሁሉ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ቀጠና እንዲሆን በጥብቅ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በውስጥና በውጭ ሆነው ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ዓላማ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ያሉ ቡድኖችንም ሆነ ግለሰቦችን በመለየት ህግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም መደገፍ እንዳለበት ጠቅሰው፤ የሃማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም