በኢትዮጵያ የሚካሄደው አካታች ብሔራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚካሄደው አካታች ብሔራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት መሰረት የሚጥል ነው
ግንቦት 20/2014 (ኢዜአ ) በኢትዮጵያ የሚካሄደው አካታች ብሔራዊ ምክክር የዴሞክራሲ ስርዓትን ለማጎልበት መሰረት የሚጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሪቪኖ ተናገሩ።
በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሪቪኖ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያና ሜክሲኮ ረዥም ዘመናትን የተሻገረ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
ሜክሲኮ በማንኛውም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን ዓለም አቀፍ የግንኙነት መርህ መሰረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮቿን በራሷ ለመፍታት አገራዊ ምክክር ለማካሄድ የጀመረችውን ጥረት ሜክሲኮ ታደንቃለች።
ምክክሩ በተለይም ሁሉንም ዜጋ ያሳተፈ እንዲሆን መወሰኑ ለዴሞክራሲ ስርዓት መጎልበት መልካም ጅማሮ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ሜክሲኮ ከባለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት አባል መሆኗንም ነው አምባሳደሩ ያስታወሱት።
ኢትዮጵያና ሜክሲኮ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዮቿ ያላትን አቋም ሜክሲኮ እንደምታከብር ተናግረዋል፡፡
ሜክሲኮ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብርና ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል የሁለቱ አገሮችን በንግድ፣ ትራንስፖርት፣ቱሪዝም፣ ግብርና እና ሌሎች የትብብር ዘርፎች ላይ ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን እየሰራች በመሆኑ ሜክሲኮ በቀጣይ በቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ በትብብር መሥራት እንደምትሻም ነው የገለጹት።
"ኢትዮጵያውያን ሜክሲኮን እንዲጎበኙ፤ በርካታ የሜክሲኮ ዜጎች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ታሪካዊና ውብ ሥፍራዎችን እንዲመለከቱ የዘወትር ህልሜ ነው" ሲሉም ዘርፉን የማጠናከር ፍላጎታቸውን ተናግረዋል።
በትራንስፖርት ዘርፍ በአፍሪካ አህጉር ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሜክሲኮ በሳምንት ሁለት ቀናት የሚበር ሲሆን ይህንን ትስስር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪ የሁለቱ አገራት ወጣቶች አብረው የሚሰሩበትን እድል ማመቻቸት፣ የትምህርት እድሎችን መስጠት፣ የቴክኒካል ትብብሮችን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያና ሜክሲኮ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ቡና፣ ሻይ፣ ቅመማ ቅመም፣ የሰሊጥ ምርትና ሌሎች እህሎችን ከምትልክባቸው አገሮች መካከል ሜክሲኮ አንዷ ስትሆን ይህም በሁለቱ አገራት መካካል ካለው የንግድ ልውውጥ በአብነት የሚጠቀስ ነው፡፡