በሀገሪቱ የእንስሳት ሀብትን ከበሽታ ለመታደግ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የእንስሳት ሀብትን ከበሽታ ለመታደግ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ተባለ
አዳማ ጳጉሜ 4/2010 በሃገሪቱ በበሽታ ምክንያት እየተጎዳ ያለውን የእንስሳት ሀብት ለመታደግ ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ በእንስሳት ጤና አገልግሎትና ቁጥጥር ዘርፍ የ2010 ዕቅድ አፈፃጸምና የተያዘው ስራ ዘመን አቅጣጫ ዙሪያ በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በውይይቱ ወቅት የግብርናና እንስሳት ሃብት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሃንስ እንዳሉት የእንስሳት ሀብት ልማቱ ዋነኛ ማነቆ ከሆኑት መካከል የውስጥና የውጭ ጥገኛ ተሃዋሲያን ቀዳሚ ነው። የቆላ ዝንብና ገንዲ በሽታ ሌላኛው የዘርፉ ተግዳሮትን ጨምሮ በእንስሳት ልማቱ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 የተካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው ሀገሪቱ በእንስሳት በሽታ ምክንያት በዓመት ከ73 ሚሊዮን በላይ ዶሮዎች፣ ፍየል፣ በግ፣ የዳልጋ ከብቶችና ግመሎች በሞት እንደምታጣ በመጥቀስ። ይህም እየባከነ ያለው የእንስሳት ሀብት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከሚያሳድረው ከፍተኛ ጫና ባሻገር አርሶና አርብቶ አደሩንም ለኪሳራ እያዳረገ ይገኛል። በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽነቱ አነስተኛ መሆንና የአርብቶ አደሩን ከቦታ ወደ ቦታ እንቅስቃሴን ታሳቢ ያደረገ የጤና አገልግሎት በሚፈለገው ልክ አለመዘርጋቱ ለእንስሳት በሽታው መስፋፋት በዋናነት ተጠቃሽ ነው። የክትባት አገልግሎትን ለማስፋፋት፣ ለሰው ኃይል ልማትና ተጓዳኝ ስራዎችን ለማከናወን በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ ጥረት ቢደረግም በዘርፉ ላይ ያመጣው ለውጥ ከተጠበቀው በታች እንደሆነ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያመለከቱት። የእንስሳትን ሀብቱን ከበሽታ በመታደግ ሀገሪቱ ከዘርፉ ልማት የተሻለ ተጠቃሚ እንድትሆን በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በልዩ ትኩረት ሊረባረቡ እንደሚገባ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር አሳስበዋል። የውይይት መድረኩም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የትግበራ ሂደት በዘርፉ ያልተሳኩ ስራዎች በቀሪ ጊዜያት ውስጥ ለመፈጸም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከርና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የተካሄደ ነው። በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር አስማማው ዱሬሳ በበኩላቸው ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታን ለመከላከል መንግስት በዓመት እስከ 60 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የክትባት አገልግሎት በነፃ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል። ባለሙያው እንዳሉት በተለይ ደስታ መሰል የበጎችና ፍየል በሽታን እንደ አውሮፓ አቆጣጠረ እስከ 2027 ከሃገሪቱ ለማጥፋት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በኦሮሚያ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ በቀለ የእንስሳት ሀብቱን ምርታማነት ለማሻሻል በመከላከል ላይ የተመሰረተ የጤና አገልግሎት በክልሉ እየተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል። ለዚህም "በተለይ በክትባት ልንከላከላቸው የምንችላቸውን በሽታዎች በዞንና በወረዳ ለይተናል" ብለዋል፡፡ ለሶስት ቀናት በተዘጋጀውና ዛሬ በተጠናቀቀው የውይይት መድረክ ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።