ሕብረተሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ተላላፊና ውሃ-ወለድ በሽታዎች እንዳይጠቃ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል

148

ግንቦት 19/2014/ኢዜአ/  ሕብረተሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ተላላፊና ውሃ-ወለድ በሽታዎች እንዳይጠቃ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቀድሞ የመለየት/ቅኝት፣ መከላከልና ምላሽ የመስጠት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ከዚህ በፊት የፖሊዮ ቫይረስ (wild poliovirus case type 1) በማሊ፤ በግንቦት ወር ደግሞ በሞዛምቢክ እንዲሁም  የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ከ19 በላይ በሆኑ አገሮች መከሰቱን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት አገራት የጤና ሥርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ መምከሩን ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሮታ ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ምዕራብ ሕዝቦችና በደቡብ ክልሎች የኩፍኝ ወረርሽኝ መከሰቱንም ነው ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው  የጠቆመው፡፡

ወባ በሚያጠቃቸው አካባቢዎችም የወባ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የትንበያ መረጃ እንደሚያሳየው በሰሜን ኢትዮጵያ ከመደበኛ በላይ ዝናብ፤ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ከመደበኛው በላይ ሙቀት፤ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ ደግሞ ከመደበኛ በታች ቅዝቃዜ ሊከሰት እንደሚችል ማመላከቱንም መግለጫው አትቷል፡፡

በዚህም በውሃ-ወለድና የመተንፈሻ አካላት እንዲሁም በነፍሳት ንክሻ የሚተላለፉ በሽታዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

በመሆኑም ሕብረተሰቡ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ ተላላፊና ውሃ-ወለድ በሽታዎች እንዳይጠቃ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባም  ኢንስቲትዩቱ አስገንዝቧል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም