የነዳጅ ግብይቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ በዘርፉ ያለውን ማነቆ መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ግብይቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ በዘርፉ ያለውን ማነቆ መፍታት እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፤ግንቦት 19/2014 (ኢዜአ)፡ የነዳጅ ማስተካከያው በህብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይፈጥርና በድጎማ የሚቀዱ ተሸከርካሪዎችም ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መከተል እንደሚገባ የደቡብ ክልል አመራሮች ገለጹ።
አሰራሩን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያስችል አሰራር እንደሚከተል የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ እንደገለጹት የነዳጅ ማስተካከያው በህብረተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንዳይፈጥርና በድጎማ የሚቀዱ ተሸከርካሪዎችም ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መከተል ይገባል።
በተለያዩ ማደያዎች ውስጥ ያለው የተበላሸ አሰራር በድጎማ የሚቀዱ ተሸርካሪዎችን የማያበረታታ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
በተቃራኒው ደግሞ የድጎማ ተጠቃሚ ተሸከርካሪዎች ህብረተሰቡን በተገቢው ከማገልገል ይልቅ በህገወጥ የነዳጅ ሽያጭ እንዳይሰማሩ በቴክኖሎጂ የታገዘ ቁጥጥር ማድረጉ ችግሩን ለመግታት አይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከትራንስፖርት በተጨማሪ ለግብርናው ዘርፍ በሚውለው ነዳጅ አቅርቦት ላይ ማስተካከያው ጫና እንዳይፈጥር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበኩላቸው በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋቱ በድጎማ የነዳጅ ግብይቱን እንዲያከናውኑ የተፈቀደላቸው ተሸርካሪዎች ነዳጁን ለታለመለት አላማ ብቻ እንዲውል ያግዛል ብለዋል።
በመመሪያ የተቀመጠው የነዳጅ ግብይት ሂደት በገቢ አሰባሰቡ ላይ የሚያመጣው ተዕእኖ እንዳይኖር መናበብ እንደሚገባም አመልክተዋል።
የተሸከርካሪዎችን መረጃ የመሰብሰብና የማደራጀት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ተወካይ ወይዘሮ ሰላማዊት ደገፉ ናቸው።
የጭነት ተሸከርካሪዎች ከድጎማ ውጭ መሆናቸው በፍጆታ እቃ ላይ ጫና ይፈጥራል የሚል ስጋት መኖሩን ጠቁመዋል።
የአነስተኛ ተሸከርካሪዎች መብዛት በነዳጅ ፍጆታ ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የጋራ ትራንስፖርቶች መጠቀም ተገቢ መሆኑን አንስተው፤ አብዛኛው የገጠሩ ነዋሪ የሚጠቀምባቸው ሞተር ሳይክሎች በመሆናቸው ቅሬታ እንዳይፈጥር የማጣጣም ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ በበኩላቸው አዲሱ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ ሲሆን ዘመኑን የዋጀ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
የቁጥጥር ስርዓቱ በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ መሆን አለበት ብለዋል፡።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ በበኩላቸው አሰራሩን በቴክኖሎጂ መደገፍ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
ፍትሃዊነቱን የጠበቀ የግብይት ስርዓት እንዲኖርና በድጎማ የሚቀርበው ነዳጅ ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል ለማድረግ ለዋና ዋና ተሸከርካሪዎች የጂፒኤስ ገጠማ ይደረጋል ብለዋል።
በክፍያ ስርዓቱ ውስጥም ቴሌ ብርን ጨምሮ ሌሎች በማሽን የሚከናወኑ የአከፋፈል ህጎችን ተግባራዊ እንደሚሆኑ ጠቅሰው፤ የሚስተካከሉ ጉዳዮችን የማስተካከል ስራ ይከናወናል ብለዋል።
ለሪፎርሙ ትግበራ ክልሎች ተገቢውን መረጃ በማደራጀትና ለሚመለከተው የፌደራል መስሪያ ቤት በመላክ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ ግብይት ሪፎርም ትግበራ ማስተዋወቂያ የውይይት መድረክ ትናንት በሀዋሳ ከተማ ማዘጋጀቱ የሚታወስ ነው።