የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ለኢትዮጵያ የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ለኢትዮጵያ የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ፈረመ

ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ኢትዮጵያ ለምታከናውነው የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች የሚውል የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ስምምነት ፈረመ።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ከግንቦት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በጋና አክራ ሲያካሂድ የነበረው ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።
የባንኩ የኃይል፣ የኢነርጂ፣ የአየር ንብረትና የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ኬቨን ካሪዩኪ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራዎች የሚውል የ830 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የድጋፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
በስምምነቱ መሰረት የገንዘብ ድጋፉ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም አስመልክቶ ከተዘጋጀው የኢንቨስትመንት ፈንድ የሚሰጥና ባንኩ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት እንደሚመራው ተገልጿል።
ገንዘቡ በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስምጥ ሸለቆ የዝዋይ-ሻላ ንዑስ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥ ተኮር የውሃ ሃብት ልማትና የኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ስራዎች ላይ እንደሚውል የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ አስታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ለባንኩ “ስትራቴጂካዊ ድጋፍ” ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ የኃይል፣ የኢነርጂ፣ የአየር ንብረትና የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት ኬቨን ካሪዩኪ ድጋፉ ባንኩ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተናዎች ፈጠራ ለታከለባቸው መፍትሔዎች የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ልማትን የመፍጠር እቅዱ አካል ነው ብለዋል።
በድጋፉ አማካኝነት ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጀክት የውሃ ደህንነትና አስተዳደር አቅምን የማጠናከር እንዲሁም በሐይቆች ላይ ያለውን ብዝሃ ሕይወት የመጨመር ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ በዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ የግብርና ስራ የሚያከናውኑ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ባንኩ በጋና አክራ ከግንቦት 15 እስከ 19 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ዓመታዊ ስብስባ ለአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ማገገም፣ የልማት ስራዎች፣ የኢኮኖሚ ትስስርና ባልተጠበቁ አደጋዎች የሚመጡ ጉዳቶችን የመቋቋም አቅም ለመገንባት ለሚያስችሉ ስራዎች ተመጣጣኝ የሆነ የልማት ፋይናንስ ማድረግ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተወያይቷል።
በግጭት፣ በአየር ንብረት ለውጥና በመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን ተጽእኖ ገምግሟል።
በዓመታዊ ስብሰባው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሬታ ሰዋሰው ኢትዮጵያን ወክለው ተሳትፈዋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረው እ.አ.አ በ1975 ሲሆን፤ እስካሁን ከ100 በላይ የኦፕሬሽን ስራዎች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ፈሰስ ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር አመልክቷል።
ባንኩ በአሁኑ ሰአት ግምታቸው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚሆኑ በትራንስፖርት፣ ኢነርጂ፣ ውሃ፣ ግብርናና የግሉ ዘርፍ ልማት ዘርፎች እየተከናወኑ ለሚገኙ 23 ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ