የደቡብ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት የጸጥታ ችግሮችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት አቅጣጫ አስቀመጠ

162

ሶዶ፣ ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) የደቡብ ክልል የጸጥታ ምክር ቤት በክልሉ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት አቅጣጫ ማስቀመጡን የክልሉ የሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ የክልሉ ጸጥታ ምክር ቤት ዛሬ  በወቅታዊ የሠላምና ደህንነት ሁኔታ ላይ ያካሄደውን ውይይት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ምክር ቤቱ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የሚያስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለአቅጣጫው ተፈጻሚነት ተቀናጅተውና ተናበው መረባረብ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

በክልሉ በየአካባቢው የሚነሱ መሠረታዊና አዳጊ ጥያቄዎች እንደሚፈቱ ገልጸው፤ በተለይ የአደረጃጀት፣ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ሕገ መንግስታዊ አሰራርን በመከተል እልባት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

የህዝቡን ጥያቄ ወደ ግጭት አጀንዳ ለመቀየር የሚጥሩ አካላትን የክልሉ መንግስት እንደማይታገስ ገልጸው፤  የሕግ ማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተለይ ታጥቀው በመሸፈት ህዝብን እያሸበሩ ባሉ አካላት ላይ  የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም