ዩኒቨርስቲው በ36 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብ ምርታማነትን ለማሳደግ እየሰራ ነው

77

ደብረ ማርቆስ፣  ግንቦት 19/2014 ( ኢዜአ) የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በ36 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የግብርና መሳሪያዎችን በማቅረብ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
 

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በሚያከናውነው ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

በዘርፉ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በተለያየ መልኩ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን በጥናት ላይ መሰረት ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እገዛዎችን ለማህበረሰብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩነ ከኋላቀር አሰራር በማላቀቅ ወደ ዘመናዊ አጠቃቀምን ተጠቅሞ ማምረት እንዲገባ ለማገዝ 12 የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በ36 ሚሊዮን ብር  ወጪ በመግዛት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን  አስታውቀዋል።

በዚህም አራት ትራክተሮች፣ አምስት የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችና አንድ የዘር መዝሪያ  ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ ግብርና መሳሪያዎችን ማቅረቡን ዘርዝረዋል።

ማሽኖቹ በኩታ ገጠምና መስኖን በመጠቀም ለሚለሙ እርሻዎች ለአርሶ አደሩ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸውን ዶክተር ታፈረ አስረድተዋል።

ዩኒቨርስቲው አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም፣ ምርጥ ዘር በማላመድ፣ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን በማቅረብ የግብርናውን ዘርፉን ለማገዝ ከሚያከናውናቸው ተግባራት  መካከል መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲው ባቀረበው የእርሻ መሳሪያዎች በመጠቀም በ1 ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት የስንዴን ሰብል 33 ኩንታል ምርት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት የማቻከል ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ስመወርቅ ካሴ ናቸው።

የእርሻ መሳሪያዎቹ በበሬ እርሻ ብዙ ጊዜ ይወስድ የነበረውን ጊዜ ከማሳጠሩም በላይ ድካማቸውን በእጅጉ እንዳስቀረላቸው ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም