ቀጥታ፡

የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ሥርዓትን በማጠናከር ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ይገባል - ማህበሩ

ዲላ ግንቦት 19/2014 (ኢዜአ..)..የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ሥርዓትን በማጠናከር በሀገሪቱ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል እንደሚገባ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበር አስገነዘበ።

ማህበሩ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "የአካባቢ ጤና የአደጋ ምላሽና ተቋማዊ መዋቅር" በሚል መሪ ሐሳብ  5ኛውን ሀገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በዲላ እያካሄደ ነው።

የማህበሩ ፕሬዝዳንትና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአከባቢ ጤና መጠበቅ ተላላፊ በሽታንና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው።

ያደጉት ሀገራት የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን በማዘመንና የአየር ብክለትን በመቀነስ እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ሰፊ ርቀት እንደሄዱ ተናግረዋል።

በሀገራችንም ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጨምሮ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የአካባቢ ጤናን ማጠናከር እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት ፕሮፌሰሩ።

በተለይ በሀገራችን በሰው ስራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለጉዳት የተዳረጉ ወገኖች አፋጣኝ የአደጋ ምላሽ እንደሚሹ ነው ያመላከቱት።

በዚህ ረገድ የጤና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለውን ሙያዊ ድጋፍ ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ለሁለት ቀናት በተሰናዳው በዚሁ ጉባዔ ላይ ከ14 በላይ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው መሆኑ ተመላክቷል።

በመድረኩ የማህበሩ አባላት፣ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ተወካዮች እና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራን እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም