በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለበሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አፋጣኝ የሕክምና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለበሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አፋጣኝ የሕክምና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል
ዲላ ግንቦት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለጉዳት የተዳረጉ ወገኖች ተላላፊ እና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ አፋጣኝ የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ።
የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን በሽታዎችን የመከላከል ተግባር አንዱ አካል ተድርጎ መታየት አለበትም ተብሏል።
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ማህበር ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን “የአካባቢ ጤና የአደጋ ምላሽና ተቋማዊ መዋቅር” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የሁለት ቀናት አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ጉባኤ ዛሬ በዲላ ከተማ ተጀምሯል።
በኢትዮጵያ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለተላላፊና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እንዳይጠቁ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ የጤና ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ የማህበሩ ፕሬዝዳንትና የጅማ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አርጋው አምበሉ ገልጸዋል።
በሽታዎችን ጨምሮ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ስራን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአየር ብክለትን መቀነስ ጨምሮ ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን ማከናወን ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የመከላከል ተግባር አንዱ አካል ተድርጎ መታየት አለበት ብለዋል።
በጉባኤው ላይ ከ14 በላይ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።