የአገር መከላከያ ሰራዊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላማዊ አማራጭን በማይቀበሉ ሽፍቶች ላይ እርምጃ ይወስዳል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላማዊ አማራጭን በማይቀበሉ ሽፍቶች ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊት ሕጋዊ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስጠነቀቁ።

ለሕግ ማስከበር መስዋዕትነት ለከፈሉ የጸጥታ አስከባሪ አካላት እውቅና የመስጠት ስነ ስርዓት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የሚገኙ አብዛኞቹ ሽፍታዎች የሰላም አማራጭን በመከተል እጃቸውን ለጸጥታ ኃይሎች እየሰጡ ነው” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በካማሺ ዞን ያለው ታጣቂ ቡድን በአገር ሽማግሌዎች አማካኝት ወደ ሰላም ለመመለስ ከተስማማ በኋላ ከሰሞኑ ወደ ጫካ የመመለስ ሁኔታ እንደታየበት ገልጸዋል።

በክልሉ ሰላማዊና ሕጋዊ አማራጭን በማይቀበሉ ሽፍቶች ላይ የሕዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል የአገር መከላከያ ሠራዊት እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን የአገር መከላከያ ሰራዊት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት በጽንፈኛ ኃይሎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሕዝቡ ወደ ልማት እንዲመለስ እያደረገ ነው ብለዋል።

በእውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ የአገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአየር ኃይል፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣ የጋምቤላና የሲዳማ ልዩ ኃይሎች እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች የማዕረግና የደረጃ እድገት እንዲሁም የሜዳሊያና ሌሎች ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከ22ኛ ንስር እግረኛ ክፍለ ጦር የተሰጣቸውን የወርቅ ሐብል ስጦታ በ”ሕግ ማስከበር” ዘመቻው ለተሰዋ የመከላከያ ሰራዊት ቤተሰብ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም በሕግ ማስከበር መስዋዕት ለሆኑ ቤተሰቦችና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም