የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል እየተሰራ ነው

ግንቦት 18/2014/ኢዜአ/ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር በዘርፉ ምርት ላይ የሚስተዋለውን ተባይ በተፈጥሮ መቀነስ የሚቻልበት ሁኔታን አስመልክቶ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ ስለሺ ጌታሁን፤ ዘርፉ ለአገር እያስገኘ ካለው ጠቀሜታ አኳያ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ በሚመለከት ማህበሩ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል።
በመንግስት በኩል የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለአገሪቱ እያስገኘ ያለውን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአምራችና ላኪነት የተሰማሩ ባለኃብቶችም አማራጮችን ለመጠቀም የተሻሉ አሰራሮችን ማመንጨትና መተግበር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እያስገኘ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አሻሽሎ ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ፤ ከግብርና ምርቶች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለመጨመር ከተባይ የፀዱ ምርቶችን ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ በሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ የተፈጥሯዊ ማዳበሪያን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዓለም ገበያ የኢትዮጵያ ምርት ተፈላጊ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በመሆኑም ምርቱን ከተባይ የመከላከያ ዘዴዎች ላይ በልዩ ትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት።
በዓለም ገበያ የሚፈለገውን የምርት የጥራት ደረጃ በመጠበቅ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ገቢን ለማሳደግ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በማህበሩ የተቀናጀ የተባይ ቁጥጥር ኃላፊ ዶክተር ዋቅቶሌ ሶሪ፤ በሆርቲካልቸር ምርቶች ላይ ተባይ የሚያስከትለውን ጉዳት እና በውጭ ገበያ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በማስመልከት ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል።