የህግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል --የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የህግ ማስከበር እርምጃው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል --የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች

ወልዲያ፣ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ) ''የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስከበር መንግስት እየወሰደ ያለውን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል'' ሲሉ በአማራ ክልል የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበሩ ተግባር ዙሪያ በወልዲያ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት እየተካሄደ ነው።
መንግሥት ህግ ለማስከበር በጀመረው ስራ በወንጀል የተጠርጠሩ ግለሰቦችን ከመያዝ ባለፈ 11 ሚሊዮን ብር ለህወሃት አሸባሪ ቡድን ሊተላለፍ ሲል በቁጥጥር ስር ማዋሉ ተገልጿል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ፈንታው አዲሱ እንዳሉት "ህገ-ወጦች ህዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ በማድረግ መንግስትና ህዝብን ለመነጠል ሲሰሩ የነበሩ በመሆኑ እርምጃው ወቅታዊ ነው።"
"የህግ ማስከበር ተግባሩ በህገወጥ ተግባር እየተሳተፉ ያሉት ላይ ብቻ ያተኮረ እንዲሆን በጥንቃቄና የህዝቡ ትብብርን ያካተተ መሆን አለበት" ብለዋል።
መንግስት ህግንና ስርዓትን ማስከበር እንዳለበት ከህዝቡ ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ህዝቡ ላቀረበው ጥያቄ መልስ የሰጠ በመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ችግሩ እስኪቀረፍ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ጎበና አባተ "ባለፉት አምስት ወራት በከተሞች ሆነ በገጠሩ አካባቢ በህዝብ መዝናኛ ቤቶች፣ በገበያ ቦታዎችና በየጎዳናው ያለአግባብ የሚደረጉ የጥይት ተኩሶች ህዝቡን ሰላም ነስቶታል" ብለዋል፡፡
በሰርግ ቤቶች፣ በቀብር ሥነ-ስርዓትና በሌሎች ማህበራዊ ክዋኔዎች በሚፈፀሙባቸው ስፍራዎች ጭምር ጥንቃቄ የጎደለው የጥይት ተኩስ በመበራከቱ በሰዎች ላይ ከአካል ጉዳት እስከ ህይወት መጥፋት አደጋ መድረሱን ጠቅሰዋል።
"ሀገሩን ከአሸባሪ ቡድን ወረራ ለመጠበቅ ግንባር ባለው የፋኖ ስም በመጠቀም በተግባራቸው ያልሆኑና የሌላ አካልን ተልዕኮ አንግበው የህዝብን ሰላም የሚነሱ አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል" ሲሊም ጠይቀዋል።
መንግስት የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ የጀመረውን የህግ ማስከበር እርምጃ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
''እኛም ወላጆች ልጆቻችንን በአላስፈላጊ ሰላምን የማወክ ተግባራት ላይ እንዳይሳተፉ በመምከር የድርሻችንን እንወጣለን'' ያሉት ደግሞ አቶ አያሌው ሲሳይ ናቸው።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ከፍያለው አበበ እንደገለጹት ሰሞኑን እየተደረገ ያለው የህግ ማስከበር ስራ መንግስት የህዝብን የሰላም ጥያቄ የመመለስ አንዱ አካል ነው።
በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሱ የህዝብን ሀብት በመዝረፍ፣ በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና መሰል ወንጀሎች ላይ እየተሳተፉ ያሉትን በመለየት ለህግ የማቅረብ ዓላማ ያደረገ የህግ ማስከበር ስራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በህግ ማስከበር ተግባሩ ላይ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን በተደረገው ጥረት በዞኑ ከ180 በላይ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ባለፉት 15 ቀናት ብቻ በቆቦ ከተማ፣ በላስታና ግዳን ወረዳዎች በኩል ወደ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሊተላለፍ የነበረ 11 ሚሊዮን ብር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉንም ገልጸዋል።
ህገ ወጦችን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ተግባሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡