የአብራሀ ባህታ የተሀድሶ ህክምና ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከል 1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የግብዓት ድጋፍ ተደረገለት - ኢዜአ አማርኛ
የአብራሀ ባህታ የተሀድሶ ህክምና ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከል 1 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የግብዓት ድጋፍ ተደረገለት

ሐረር፤ ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ) በሐረር ከተማ የሚገኘው የጁገል ሆስፒታል ለአብረሃ ባህታ የተሀድሶ እና ሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ ማምረቻ 1 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የአካል ድጋፍ ህክምና መስጫ ማሽኖችን አበረከተ ።
ማዕከሉ ለሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ህክምና ለሚፈልጉ ተገልጋዮች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከጁገልና ሂወት ፋና እስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ሪፈር ተፅፎላቸው ለሚመጡ ተገልጋዮች አገልግሎት የሚሰጥ ነው።
ማሽኖቹ በማዕከሉ የሚሰጠውን ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ህክምና አገልግሎት ለማሳለጥ አስተዋፆ እንደሚኖራቸው ተገልጿል።
ድጋፉን ያደረገው ጁገል ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ኢብራሂም ሳሊህ የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ገልጸው፤ አገልግሎቱ በክልሉ መጀመሩ ለህብረተሰቡ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል።
የአገልግሎት ፈላጊዎችን እርካታ ለማሳደግና ማዕከሉን ማጠናከር በማስፈለጉ ማሽኖቹን በድጋፍ መልክ ለተቋሙ ማበርከታቸውን ገልጸዋል ።
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃለፊ አቶ ፈትሂ ማህዲ በበኩላቸው ካሁን ቀደም አገልግሎቱ ይሰጥ የነበረው በአንድ ማሽን በመሆኑ የፈዝዮቴራፒ አገልግሎት ፈልገው ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ተገልጋዮች ተራ ለመጠበቅ ይገደዱ እንደነበር ገልጸዋል ።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ ተጨማሪ ማሽኖች በድጋፍ መገኘታቸው የማዕከሉን አገልግሎት ቀልጣፋና የተሳለጠ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚኖራቸው ገልጸዋል።
''ተጨማሪ ማሽኖች ያስፈልጋሉ'' ያሉት አቶ ፈትሂ፤ ተቋሙን በሙሉ አቅሙ ወደ አገልግሎት ለማስገባትና ሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፎችን ለማምረት የግብዓት እጥረት ማጋጠሙን ጠቁመዋል።
ችግሩን ቀርፎ ተቋሙን በሙሉ አቅሙ አገልግሎቱን ለማስጀመር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።