በከተማው በተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማው በተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ ነው
ደሴ፣ ግንቦት 18/2014 (ኢዜአ) በደሴ ከተማ አስተዳደር የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በኅብረተሰቡ በመደገፉ ተጨባጭ ውጤት በማምጣቱ አንፃራዊ ሰላም እየሰፈነ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማው አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በከተማው እየተካሄደ ባለው ሕግ ማስከበር ዘመቻ ዙሪያ ለጋዜጠኞች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ምክትል ከንቲባው በመግለጫቸው በከተማው ወንጀሎች እየተበራከቱ ከመምጣታቸውም ባለፈ የኅብረተሰቡ የህልውና ጉዳይ ለከፍተኛ ስጋትና አደጋ ተጋልጦ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
መንግሥት ነገሮችን በሂደት ሊስተካከሉ ይችላሉ በሚል እምነት በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት ቢያሳልፋቸውም አጥፊዎቹ ከድርጊታቸው ባለመቆጠብ የፀጥታ ስጋቱ የበለጠ እየባሰ መምጣቱንም ገልፀዋል።
በዚህም ኅብረተሰቡ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ከመቆየቱም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይ ተዋዶ፣ ተዋልዶና ተከባብሮ በአንድነት በፍቅር የሚኖረውን ሕዝብ በኃይማኖት ሽፋን ለማጋጨት ከፍተኛ ሴራ ተወጥኖ እንደነበረ አስታውሰው፤ ሴራውን በቅንጅት ማክሸፍ ተችሏል ብለዋል።
በመሆኑም የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ፣ ሀገር ለማስቀጠልና ጠላትን በተደራጀ አግባብ ለመመከት መንግሥት ሕግ የማስከበር ዘመቻው በቅንጅት መጀመሩን አቶ ሳሙኤል አስታውቀዋል።
በከተማዋ ባለፈው አንድ ሳምንት በተደረገ ጠንካራ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተስፋ ሰጭ ሰላም እየመጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ኅብረተሰቡም ለሕግ የማስከበር ዘመቻው ውጤታማ እንዲሆን በወንጀል የተጠረጠሩትን በመጠቆም፣ በማጋለጥ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በቅንጅት በመስራት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀን ጭምር ግድያና ዝርፊያ ተጀምሮ እንደነበረ ጠቁመው፤የግድያ፣ የሽብር፣ የዝርፊያ፣ የኮንትሮባንድ ንግድና የጥይት ተኩስ ወንጀሎች እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ እስካሁን በተደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ከ100 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘመቻው ንጹሃንም ያለ አግባብ እንዳይያዙ ከህብረተሰቡ ጋር በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስም ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።
የሕግ ማስከበር ዘመቻውን ለማደናቀፍ በማህበራዊ ሚድያን ጨምሮ በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች መንግሥት ትጥቅ እያስፈታ ነው፣ በጅምላ እያሰረ ነው በሚል የሚናፈሰው መሰረት የሌለው የጠላት ወሬ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለዚህም የኃይማኖት አባቶች ጭምር እምነት የወንጀለኛ መደበቂያ እንዳይሆን ተጠርጣሪዎችን አሳልፈው እየሰጡ መሆኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ነፍስ ገዳዮች፣ የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎችና ሰላምን የማይፈልጉ ፅንፈኞች ሁከትና ብጥብጥ የገቢ ምንጫቸው በመሆኑ ህግ እንዲከበር አይፈልጉም ብለዋል።
አቶ ሳሙኤል አክለውም አጥፊዎቹ ካሉበት እየተለቀሙ ወደ ህግ በመቅረባቸው "ከተማችን ሰላም እየሆነች ነው" ሲሉ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡ በሴራ ፖለቲከኞች ሳይታለል አንድነቱንና ሰላሙን ከምንጊዜውም በላይ በማጠናከር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እንዲጠብቅም አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጎን በመሆን መረጃ በመስጠት፣ አጥፊዎችን በመጠቆም እያደረገ ያለውን ጠንካራ ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።