የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው

158

ግንቦት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን በማዘመን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እያዳመጠ ነው፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት አስር ወራት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ዘርፉን ለማዘመን ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

ከዚህ ውስጥም የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ የአሰራር እና የሰው ኃይል ጉድለቶችን በማሟላት የተሻለና ዘመናዊ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት።

የተቀናጀ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽነት የማሳደግ፣ የሎጂስቲክስ ትራንስፎርሜሽን የማረጋገጥና የማዘመን ስራዎችም እንዲሁ በዚሁ ወቅት ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት መሆኑን   ገልፀዋል።

የትራፊክ ደሕንነትና ማኔጅመንትን የማሻሻል፣ ዘርፉ ለአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲጓዝ ማድረግ የሚያስችል አቅም የመፍጠር ስራዎችንም ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀዋል።

በቀጣይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልዩ ትኩረት በሚሹ በመልካም አስተዳደር እና አገልግሎት አሰጣጥ ጉዳዮች በስፋት ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱንም ነው ወይዘሮ ዳግማዊት የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም