ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው የቆዩ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ ተጀመረ

107

ደሴ ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በፀጥታ ችግር ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው የቆዩ ወገኖችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ መጀመሩን የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ይመር ለኢዜአ እንደገለጹት ከተለያዩ አካባቢዎች በፀጥታ ችግር  የተፈናቀሉ ከ35 ሺህ በላይ ወገኖች በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

አብዛኛው ተፈናቃዮች ከኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢውች በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተፈናቀሉ መሆናቸውን ገልጸው፤ ወደ ቀድሞ ቀያቸው ለመመለስ የአማራና የኦሮሚያ ክልል አመራሮች በየደረጃው ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ችግር በነበረባቸው አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ተፈናቃዮችን በነበሩበት ቦታ መልሶ ለመቋቋም በተደረሰው ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ ተፈናቃዮችን የመመለስ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

አስተማማኝ ሰላም በሰፈነባቸው አከባቢዎች ከ2 ሺህ 800 በላይ ተፈናቃዮችን በቅርቡ ለመመለስ መታቀዱን ጠቅሰው በዛሬው እለት ከ900 በላይ የሚሆኑትን መሸኘት ተጀምሯል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን በደብረብርሃን ከተማ ተረክቦ በመውሰድ በየቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የክረምቱ ወቅት በመቃረቡ ፈጥኖ እንዲመለሱ በማድረግና ሰብል ማምረት እንዲችሉ የእርሻ በሬና ግብአት ከማሟላት ባለፈ በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም ወስኖ ወደ ተግባር መግባቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞኑ በሚችለው አቅም ተፈናቃዮቹ እንዲቋቋሙ እንደሚደግፍ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ እስካሁን ላደረገው ትብብርና እንክብካቤ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከተፈናቃዮች መካከል አቶ አባተ አሊ በሰጡት አስተያየት በፀጥታ ችግር ምክንያት 6 ቤተሰብ ይዘው ተፈናቅለው በደቡብ ወሎ ዞን ተጠልለው መኖር ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡

ሙሉ ንብረታቸውን ትተው በመፈናቀላቸው ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደነበረ አስታውሰው፤መንግስትና ህብረተሰቡ የእለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ በማቅረብ ላደረጋለቸው ድጋፍም አመስግነዋል።

አሁን ቤተሰብ መስርተው ሲኖሩበት በነበረው አካባቢ ሰላም ሰፍኖ እንዲመለሱ በመደረጋቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ዳግም ተመሳሳይ ችግር እንዳይከሰት መንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድና አስከፊ ችግር በኋላ በአካባቢያችን ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀያችን ለመመለስ በመብቃታቸው መደሰታቸውን የገለጹት ከጅማ ዞን የተፈናቀሉት ወይዘሮ ጦይባ መሃመድ ናቸው፡፡

"እድሜ ልኬን ያፈራሁትን ሙሉ ንብረት ትቼና 5 ቤተሰብ ይዤ እንድፈናቀል ያደረገኝ የኦሮሚያ ህዝብ ሳይሆን የሴራ ፖለቲከኞችና ሸኔ ናቸው" ያሉት ወይዘሮዋ በዘላቂነት እንድንቋቋም መንግስት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

ተፈናቅለን ከአንድ ዓመት በላይ ብናስቆጥርም መንግስት ህብረተሰቡን አስተባብሮ ልጆቻቸው መጥፎ ስሜት እንዳይሰማቸው በማድረግና የምግብ ችግር እንዳይገጥማቸው ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

የእርሻ በሬዎቻቸው ጭምር በዘራፊዎች መወሰዳተውን ገልጸው የመኸር ወቅቱ በመሆኑ የግብርና ስራቸውን እንዲያከናውኑ ፈጥኖ አስፈላጊው ድጋፍ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።

"ሰላምና አንድነታችን በጋራ ጠብቀን መለወጥ እንጅ እርስ በእርሳችን እየተናቆርን ሀገራችንን ለጠላት አሳልፈን መስጠት የለብንም" ሲሉ ተፈናቃዮቹ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም