የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ ገብተዋል

77

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የተኩስ አቁም ውሳኔውን መንግስት ካሳለፈ ወዲህ አምስተኛ ዙር የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸውን አስታወቀ።

ዛሬ ከሰዓት ተሽከርካሪዎቹ ወደ ከተማው መግባታቸውንና እርዳታው ተደራሽ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ትብብር ማድረጋቸውን አመልክቷል።

ተሽከርካሪዎቹ የሕክምና ግብአቶች፣ የውሃ ማከሚያ አቅርቦቶችና ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን መያዛቸውን ገልጿል።

በተያያዘ ዜና የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ትናንት በአፋር ክልል ሰመራ በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዘጠኝ ሺህ ተፈናቃዮች ለአንድ ወር የሚሆን የምግብ ድጋፍ እንዳደረገ አስታውቋል።

ዱቄት፣ ጥራጥሬዎችና ዘይት ከተደረጉት ድጋፎች መካከል እንደሚገኙበትም ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም