አመራሩና ሰራተኛው ማህበረሰቡን በማገልገል ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

102

ባህር ዳር፤ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል በየደረጃው ያለው አመራርና የመንግስት ሰራተኛ ሃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ጌታቸው ጀንበር ( ዶ/ር) አሳሰቡ።


በአገልግሎት አሰጣጥና በወቅታዊ ጉዳዮች  ዙሪያ  በባህር ዳር ከተማ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።



ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ያካሄደውን ወረራ ተከትሎ የአገልግሎት አሰጣጡ ተስተጓጉሎ ቆይቷል።

ባልተወረሩ የክልሉ አካባቢዎችም በተፈጠረው ሁኔታ ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት ተፈጥሮ እንደነበርም ገልጸዋል።

በመሆኑም በየደረጃው ያለው አመራርና የመንግስት ሰራተኛ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ አገልግሎት በመስጠት ሃላፊነቱን  መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ባንች አምላክ ገብረ ማሪያም በበኩላቸው ባለው የሰው ሃይልና በሚመደበው በጀት ተገቢውን አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።



የመንግስት ሰራተኛው  ሃላፊነቱንና ግዴታውን ተረድቶ ህብረተሰቡን ከማገልገል አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።

መድረኩ  አመራሩና ሰራተኛው ተቀራርበውና ተቀናጅተው የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ  የሚሰሩትን ለማበረታታትና ያልሰሩትን ደግሞ ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በምክክር መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራርን ጨምሮ፣ በየደረጃው የሚገኘው  አመራርና የመንግስት ሰራተኞች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም