በህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

94

ባሌ፤ ግንቦት 17/2014 (ኢዜአ)፡ በባሌ ዞን በህገ ወጥ የህጻናት ዝውውር የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦችን በ18ና በ10 ዓመት ጽኑ እስራት መቅጣቱን የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈባቸው የምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ ወረዳ አባሮ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑት አቶ ጀማል ቱሳና አቶ ህርጶ ዲማ ላይ መሆኑ ተገልጿል።

ግለሰቦቹ በእስራት የተቀጡት ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ 13 ህጻናትን በህገ ወጥ መንገድ ከምዕራብ አርሲ ወደ ባሌ ዞን ሲናና ወረዳ "ኦቦረ" ቀበሌ ሲያዘዋውሩ እጅ ከፍንጅ በመያዛቸው መሆኑ ተመላክቷል።

ግለሰቦቹ የተከሰሱበትን ወንጀል እንዲከላከሉ ዕድል ቢሰጣቸውም መከላከል አለመቻላቸውን  የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አብዱራዛቅ አብዱልቃድር በችሎቱ ላይ ተናግረዋል።

ወንጀሉን መፈጸማቸውን በአቃቤ ህግ በመረጋገጡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሸ አቶ ጀማል ቱሳ በ18 ዓመት፣ 2ኛ ተከሳሽ የሆኑትን  አቶ ህርጶ ዲማን ደግሞ በ10 ዓመት ጽኑ እስራት መቅጣቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም