የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምርምርና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲውን በማጠናከር ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና በቴክኖሎጂ ፈጠራ እገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
30ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ''ምርምር የማህብረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመልሶ መቋቋምና ዕድገት’’ በሚል መሪ ቃል ዛሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ''ተለዋዋጭ የሆነው የአለም ኢኮኖሚ በሀገራችን ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ለመቋቋም በጥናትና ምርምር የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ ወሳኝ ሚና አለው'' ብለዋል።
ሚኒስቴሩ የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ ሽግግርና ፈጠራ ለማጠናከር የሚያግዙ ስትራቴጂና ፖሊሲዎችን በመንደፍ ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪ ለመሆን እንዲቻል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና በቴክኖሎጂ ሽግግር የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢኒያም ጫቅሉ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በኮቪድ ወረርሺኝና በአካባቢው ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉባኤው በወቅቱ አለማካሄዱን ጠቁመዋል።
በምርምር ጉባኤው ከ100 በላይ የምርምር ስራዎችና ከ20 በላይ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች የሀገርን እድገትና ብልጽግና በማረጋገጥ ረገድ የጎላ ድርሻ እንዳላቸው ያመለከቱት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳሁን ተገኘ ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት አመታት ለምርምር ስራዎች መሳለጥ ከ138 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ ጥራታቸውን የጠበቁ የምርምር ስራዎች እንዲከናወኑ ድጋፍ ማድረጉንም አስታውሰዋል።
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃፊዎችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፤ተመራማሪዎች፣መምህራንና ተማሪዎች እየተሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️