12ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

63

ግንቦት 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) 12ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽንና ገበያ ልማት ማዕከል ሊካሄድ ነው።

የንግድ ትርኢቱ ከግንቦት 25 እስከ 29/2014 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ተጠባባቂ ዋና ጸኃፊ ውቤ መንግሥቱ በሰጡት መግለጫ፤ የንግድ ትርኢቱ የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ ለማቀራረብ ያለመ ነው ብለዋል።

በዘርፉ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ግብ እንዳለው ጠቁመው በንግድ ትርኢቱ የአቻ ለአቻ የንግድ መድረክና የፓናል ውይይቶች እንደሚኖሩም ገልጸዋል።

የገበያ ትስስር፣ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ጥምረት እንዲሁም በአገር ውስጥና በውጭ አምራቾች መካከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እድል እንደሚፈጥርም ነው የተናገሩት።

በሥራና ክህሎት ሚንስቴር የገበያ ጥናት ዳይሬክተር ዘሪሁን አለማየሁ በበኩላቸው ሚንስቴሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ኢንተርፕራይዞች በንግድ ትርኢቱ ይሳተፋሉ ብለዋል።

ይህም ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያቀርቡ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የንግድ ትርኢቱ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከሥራና ክህሎት ሚንስቴር ጋር በመተባበር እንደሚዘጋጅ ተጠቁሟል።

የንግድ ትርኢቱ "የኢትዮጵያን ይግዙ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ" በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም