ቀጥታ፡

የክልሉ ህዝብ በአዲሱ ዓመት ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል ጠንክሮ መስራት አለበት--- ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት

ጋምቤላ ጷጉሜ 4/2010 ህዝቡ አንድነቱን በማጠናከር በአዲሱ ዓመት የክልሉን ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ጠንክሮ እንዲሰራ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ቱት ጥሪ አቀረቡ። አዲሱን ዓመት በማስመልክት ርዕሰ መስተዳድሩ ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈዋል። ርዕሰ መስተዳደሩ አዲሱን ዓመት አስመልክተው እንደተናገሩት ባለፈው ዓመት የክልሉን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማስቀጥል  ረገድ መልካም ተግባራት ተከናውነዋል። የክልሉ መንግስት በአዲሱ ዓመት ያለውን ሰላምና የህዝቦች አንድነት በማስጠበቅ ያልተፈቱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ምላሽ ለመሰጠት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። ህዝቡ በቀጣዩም  ዘመን በአዲስ መንፈስ አንድነቱን አጠናክሮ ለክልሉ እድገትና ብልጽግና በርትቶ መስራት አለበት። በተለይም እንደ ሀገር የመጣውን ለውጥ በማስቀጠል ለክልሉ ዘላቂ ሰላምና ልማት መሳካት ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። ለስኬታማነቱ በተለይም በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት እንደ ሀገር የተጀመረውን ለውጥ እውን በማደረግ ህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል። የዘንድሮው አዲስ ዓመት በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሰላም፣ የፍቀር፣ የመደመርና የእድገት ለውጥ በተጀመረበት ወቅት የሚከበረ በመሆኑ ልዩ ያደረገዋልም ብለዋል። የክልሉ ህዝብ የቆየውን የአብሮነትና የመደጋገፍ እሴቱን በሚያጎለበት መልኩ በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፍም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አዲሱ ዓመት ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም