የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ግንቦት 16/2014 (ኢዜአ)  በአንዳንድ የዓለም አገራት የተከሰተውን የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

መንኪ ፖክስ በተሰኘው ቫይረስ የሚከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በምዕራብ አፍሪካ ሲሆን አሁን ላይ በሽታው ከ50 ዓመት በኋላ በምዕራቡ ዓለም ዳግም ብቅ ብሏል።    

በሽታው በሰውነት የመቁሰል አደጋ የሚያስከትል ሲሆን በሽታው በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ወይም እንሰሳት ጋር በሚኖር ንክኪ ሊዛመት እንደሚችል ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።

እስካሁን ስፔን፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ካናዳ፣ አሜሪካና አውስትራሊያ ቫይረሱ የተገኘባቸው አገራት ሆነዋል።

በእነዚህ አገራት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች 92 የደረሱ ሲሆን ሌሎች አገራት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።    

ይህንንም ተከትሎ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ለመከላከል የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለኢዜአ የገለጸው።  

በኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቅና የመረጃ ሥርዓት አስተዳደር ዳይሬክተር ዘውዱ አሰፋ፤ ኢትዮጵያ የበሽታውን ሥጋት ለመቀነስ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወነች ነው።

በተለይም ኅብረተሰቡ ስለ ቫይረሱ በማስተማር በሽታውን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መጀመራቸውን ነው የገለጹት።

በዚህም ዜጎች ወደ ተለያዩ አገራት ጉዞ ሲያደርጉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ለተጓዦችና ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቫይረሱ ቢከሰት እንኳን በቀላሉ ለመቆጣጠር ለትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና ተጠቃሚዎች ለሕክምና ባለሙያዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራው እየተሰራ ነው ብለዋል።  

ጎን ለጎንም አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር በሚያገናኙ ድንበሮች ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲደረግ የቅኝት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አቶ ዘውዱ የተናገሩት።

በዝንጀሮ ፈንጣጣ የተያዙ ሰዎች መጀመሪያ ላይ ሙቀት፣ ራስ ምታት፣ የጀርባ ሕመም፣ የጡንቻ ሕመም፣ የሰውነት አልፎ አልፎ ማበጥና በማንኛውም ነገር ላይ ፍላጎት ማጣት ይታይባቸዋል።

ሕመሙ በራሱ ጊዜ የሚጠፋ ሲሆን ከ14 እስከ 21 ቀናት  እንደሚወሰድበት መረጃዎች ያመለክታሉ።

ኅብረተሰቡ የበሽታውን ምልክቶች በሚያይበት ጊዜ በቅርቡ ላለው ጤና ተቋም እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር በ8335 እንዲያሳውቅ ኢንስትቲዩቱ ጠቁሟል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም