በአዲስ አበባ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 77 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

102

ግንቦት 16/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽህፈት ቤት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 77 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ወሰደ።

የየካ ክፍለ ከተማ በኑሮ ውድነትና መፍትሄው ዙሪያ በክፍለ ከተማው ከሚኖሩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ከፍሎች ጋር ውይይት አድርጓል።

የከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አበባው ደመቀ እንደገለጹት፤ በክፍለ ከተማው ኑሮን ለማረጋጋት የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።  

ይህንንም ተከትሎ ያልተገባ ዋጋ በመጨመር የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ያደረጉ 77 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ነው የተናገሩት።   

በሌላ በኩል የገበያ መዳረሻዎችን ከማስፋት አኳያ ቀድሞ ከነበሩት አራት የገበያ ቦታዎች ወደ 12 ከፍ እንዲሉ መደረጉን ጠቁመዋል።  

ከመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች አኳያም ከሦስት አቅራቢዎች ጋር ትስስር በማድረግ በየወሩ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።  

የውይይቱ ተሳታፊዎች በዋጋ ጭማሪና መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በሚደብቁ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የቁጥጥር ሥርዓቱና የሕግ ተጠያቂነት የማስፈን ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የሸማች ማኅበራትም የተረከቡትን የፍጆታ እቃዎች ያለ አድልዎ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

በከተማው የተጀመረው የእሁድ ገበያ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

በውይይቱ የተነሱ ኃሳቦች በግብዓት በመውሰድ በቀጣዮቹ ወራት ለተፈጻሚነታቸው እንደሚሰራ የክፍለ ከተማው ንግድ ጽህፈት ቤት አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም