የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 720 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአልሚ ምግብ ድጋፍ መርሃ-ግብር በይፋ አስጀመረ

87

ግንቦት 16/2014/ኢዜአ/ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ 720 ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአልሚ ምግብ ድጋፍ መርሃ-ግብር በይፋ አስጀመረ፡፡

ድጋፉ በከተማ ደረጃ የተጀመረው የቀዳማዊ ልጅነት እድገት መርሃ-ግብር አካል መሆኑም ታውቋል።

ድጋፉም በዋናነት ጨቅላ ህጻናትን፤ አጥቢ እናቶችን  እንዲሁም ነፍሰጡር ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተገለጸው፡፡

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሀብታሟ ቡልቻ እንደገለጹት፤ መርሃ ግብሩ በከተማ ደረጃ የተጀመረውን የቀዳማዊ ልጅነት እድገት ፕሮጀክት አካል ነው፡፡

መርሃ ግብሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ከተማ ክፍለከተማ በይፋ መጀመሩን ገልጸው፤ በዚህም በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ 720 ዜጎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ነው ያሉት፡፡

ድጋፉ በዋናነት ህጻናት በአካልና ስነ-ልቦና ብቁ ሆነው እንዲያድጉ የሚያግዝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

መርሃ ግብሩ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ፤ተጠቃሚዎቹ በተዘጋጀላቸው ኩፖን አማካኝነት በክፍለከተማው በሚገኙ በሁለት ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የድጋፉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡

ድጋፉ ከተደረገላቸው እናቶች መካከል ወይዘሮ ገነት ገዛኸኝ እና ወይዘሮ ዘይነባ ሲራጅ በበኩላቸው መንግስት የኑሮ ሁኔታቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ላደረገላቸውን ድጋፍ አመስግነው፤ድጋፉ በሌሎች አካባቢዎችም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም