ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በታሪክ ትምህርት ላይ የተፈጠረውን ተቃርኖ ማረቅ ይገባል - የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ

ግንቦት 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር በታሪክ ትምህርት ላይ የተፈጠረውን ተቃርኖ ማረቅ እንደሚገባ የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ገለጹ።

ከአንድ ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ከሰላም ሚኒስቴርና ዴስትኒ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር "ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የታሪክ ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት የታሪክ ኤምሬተስ ፕሮፈሰር ባህሩ ዘውዴ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ሙያዊ ታሪክ አፃፃፍ የተጀመረው ከስልሳ ዓመት በፊት በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነበር።

የኢትዮጵያ ታሪክ ሙያዊ አፃፃፍን መከተል ከጀመረ 60 ዓመታትን ያስቆጥር እንጂ በዜጎች ዘንድ ተጽዕኖ መፍጠር አልተቻለም ብለዋል።

በዚህ የውይይት መድረክ ላይም የኢትዮጵያ ታሪክ አፃፃፍ ጉዞ፣ ለጀማሪ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለመስጠት በታሰበው የታሪክ ትምህርት፣ በታሪክ ላይ በተፈጠረው ተቃርኖና በሌሎች ታሪክ ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ አመልክተዋል።በመሆኑም ታሪክ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የጎላ ሚና ስላለው ተቃርኖዎችን ለመፍታት የሚያስችል ኢትዮጵያን የሚወክል ታሪክ መፃፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

May be an image of 7 people, people sitting and indoor

በኢትዮጵያ በአብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ማስተማር ቢቻልም በታሪክ አረዳድ ላይ ያለውን ልዩነት ማጥበብ አልተቻለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ፈተና የበዛበት መሆኑን ገልጸው፤ “አልጋ በአልጋ የሆነ የሀገረ መንግስት ግንባታ የተደረገበት የዓለም ሀገር የለም” ብለዋል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው በኢትዮጵያ ታሪክ በትርክት እየተተካ ዜጎች የሀገራቸውን ታሪክ በትክክል እንዳይረዱ አድርጓል ብለዋል።

May be an image of 1 person, standing and indoor

በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ መምከርና ጥልቅ ውይይት አድርጎ መግባባት ላይ ካልተደረሰ አሁን ያለውን ሀገራዊ ችግር መፍታት አይቻልም ብለዋል።

የተዛባ የታሪክ አረዳድና ታሪክን በትርክት መቀየር ለሀገራዊ ውድቀታችን መነሻ ሆኗል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋናው ብልሽትም ከታሪክ አተያይ የሚመነጭ መሆኑንም ገልጸዋል።

ትውልዱ ታሪክን በሚገባ መንገድ አውቆ ሀገርን ለማሻገር የሚያስችል የታሪክ እውቀት እንዲኖረው የታሪክ ምሁራን መምከርና ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም