ቢሮው ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቢሮው ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ነው
አዳማ፣ ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ የስራ ፈጠራ ክህሎትና ቴክኖሎጂን በማስፋፋት ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ቢሮው የስራ ፈጠራ ክህሎትና ቴክኖሎጂን ማስፋፋት በሚቻልበት ሂደት ላይ ከዩኒቨርስቲ ሙሁራንና ኮሌጆች ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ መክሯል።
ቴክኖሎጂን መጠቀምና ማስፋፋት የዜጎችን የስራ ፈጠራ ክህሎት በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው የቢሮው ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።
የወጣቶችን የፈጠራ አቅም ከማሳደግ ባለፈ በርካታ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጣሪ እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ተወዳዳሪ ለመሆን ፈጠራና ሙያን አቀናጅቶ ማሳደግ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ለዚህም ቴክኖሎጂን ማስፋፋትና ማጎልበት ይገባል ብለዋል።
የስራና ክህሎት ሰልጣኞች ተገቢውን ዕውቀት እንዲጨብጡ ቢሮው ከ860 በላይ የስልጠና ደረጃዎች ማዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የቢሮው ኃላፊ አክለውም ሰልጣኞች ደረጃ በደረጃ ወደ ኮሌጆች ተልከው ስልጠና እየገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የትምህርትና ስልጠና ትስስር ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የክልሉ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ኮሚሽነር ዶክተር አብዱልአዚዝ ዳውድ እንዳሉት ክህሎትና ቴክኖሎጂን ማገናኘት የሚችል የሰው ኃይል መገንባት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች ይጠበቃል።
ገቢ ምርቶችን በሀገር ምርት መተካት የሚቻለው ክህሎትና ቴክኖሎጂን በማገናኘት ጥራት ያለው የፈጠራ ችሎታ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል መፍጠር ሲቻል እንደሆነም ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ እንዳሉት ይህን መተግበር የሚቻለው የፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች አሁናዊ ሁኔታን በትክክል ተገንዝበው በፈጠራና ቴክኖሎጂ ማላመድና ማስፋት ላይ በትኩረት ሲሰሩ ብቻ ነው።
የኦሮሚያ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ የስልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ከማል የመወያያ ጽሑፍ ቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ኃላፊው ባቀረቡት ጽሑፍ እንደገለጹት በአዲሱ የስራና ክህሎት ስልጠና ስትራቴጂ ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ 70 በመቶ በተግባር የተደገፈ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በዚህም ከ220 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በአዲሱ የስልጠና ሥርዓት ወደ ስራ እንዲገቡ ተገቢውን የአቅም ግንባታ ስራ ተጠናቆ ሰልጣኞች እንዲቀበሉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።