የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በግጭት ነጋዴዎች ከደረሰባቸው ጥፋት ትምህርት በመውሰድ ለከተማዋ ሰላም የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ ነው

92

ግንቦት 15/2014/ኢዜአ/  የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም በግጭት ነጋዴዎች ከደረሰባቸው ጥፋት ትምህርት በመውሰድ ለከተማዋ ሰላምና ልማት የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ መሆኑን የከተማዋ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

ከዚህ ቀደም በሻሸመኔ ከተማ የጥፋት ኃይሎች በሸረቡት ሴራ ምክንያት በርካታ ዜጎች ለዘመናት ያፈሩት ሃብትና ንብረት መውደሙ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም በርካታ መንግስትና የሕዝብ ሃብት መውደሙ የሚታወስ ሲሆን፤ ነገር ግን የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማዋን በአጭር ጊዜ መልሶ በመገንባት ረገድ ውጤታማ ሥራ ማከናወናቸው ይገለጻል፡፡  

ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ከንቲባ ወሾ ከድር የሻሸመኔ ከተማ ከየትኛውም አካባቢ የመጡ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ነው የሚናገሩት፡፡

በተጨማሪ ከተማዋ "ራስ ተፈሪያን" በመባል የሚታወቁ የጃማይካ ዜጎችንም አቅፋ የምታኖር መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

ሆኖም የሕዝቡን አብሮ የመኖር እሴት ማጥፋት በሚሹ አካላት ከዚህ ቀደም የጥፋት ሴራ በመጠንሰስ በከተማዋ የማያባራ ግጭት ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ ለነበረው ችግር ሁሉ መንስኤ ጥቅማቸው የተነካባቸው የግጭት ነጋዴዎች እንጂ በሕዝብ ዘንድ ምንም አይነት ጥላቻ እና ቂም እንዳልነበር ነው የጠቆሙት፡፡

ነገር ግን የከተማዋ ነዋሪዎች አንድነታቸውን ጠብቀው የግጭት ነጋዴዎችን ሴራ በመመከት በከተማዋ ለመፍጠር የታቀደውን የማያባራ ግጭት ማክሸፍ መቻላቸውን ነው ያስታወሱት፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች ከገጠማቸው ችግር ትምህርት በመውሰድና  እጅ ለእጅ ተያይዞ በመሥራት ሻሸመኔን ዳግም ወደ ልማትና ሰላም መመለስ ችለዋል ነው ያሉት፡፡

"የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ላይ ሰላማቸውን በጋራ እየጠበቁ ነው፤ ሴረኞች ለጥፋት ዓላማቸው ዳግም ዕድል ማግኘት አይችሉም " ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ ቢሆንም፤ በሂደቱ በርካታ ፈተናዎች ማጋጠማቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህን ፈተናዎች በመሻገር ረገድ ደግሞ ኀብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ከፍተኛ ሚና ማበርከቱም ይገለጻል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም