ቀጥታ፡

ቀጣዩ ዓመት ለውጡን የምናጠናክርበትና የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እውን የምናረደርግበት ነው-የፖለቲካ ፓርቲዎች

አዲስ አበባ ጳግሜ 4/2010 አዲሱ አመት ለውጡን የምናጠናክርበትና የህዝብ የስልጣን ባለቤትነት እውን የምናደርግበት ዓመት ነው ሲሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። አሁን በተጀመረው የለውጥ አንቅስቃሴ መንግስት በርካታ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብትና ተያያዥ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እየሰራ ያለ ቢሆንም ከሁሉም በላይ ግን የብሄራዊ መግባባትና አገራዊ አንድነት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ኢዜአ ያነጋገራቸው ፓርቲዎች ተናግረዋል። ቀጣዩን አዲስ ዓመት ለየት የሚያደርገው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለህዝብ የሚሰራና በሀዝብ የሚደገፍ መንግስታዊ መዋቅር እየመጣ መሆኑና በአዲስ መንፈስ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እራሳችንን የምናዘጋጅበት መሆኑ ነው ሲሉም ተናግረዋል። ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች መካከል ዶክተር ጫኔ ከበደ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ፕሬዝዳንት ቀጣዩ ዓመት  በተቃዋሚውም በኩል ፖለቲካው መስመር እንዲይዝ ከተፈለገ የተጀመረው የብሄራዊ መግባባት ድርድር ፣ እርቀ ሰላምና በህጎች ዙሪያ ላይ በመነጋገር  ለትውልድ የሚሆን  አሳታፊ ፖለቲካ  እንዲ መሰረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡   አቶ ለገሰ ተፈራ የሰማያዊ ፓርቲ የብሄራዊ መግባባትና እርቅ ጉዳይ ኃላፊ ከዚህ በኋላ አገሪቱ የምትተዳደረው በምርጫና  በህዝብ ይሁንታ እንዲሆን ከሌሎች ተባባሪ አካላት ፣ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ጋር ተባብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡  ከዚህ በተጨማሪም አብዘሃኛው የኢትዮጵያ  ህዝብ ወጣት እንደመሆኑ አሁን የመጣውን አገራዊ ለውጥ በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ በማየት ለፍሬ ማብቃትን ይጠይቃል ሲሉም ተናግረዋል። የፖለቲካ አመራሩና አገርን የማስተዳደር ኃላፊነቱንም ወጣቱን እያበቁ በመተካካት ለልማትና ለሰላም የምንሰለፍበት ሊሆን ይገባልም ብለዋል። ፓርቲዎቹ በዚህ ረገድ አቅደው ወደ ስራ እየገቡ መሆኑንና ህዝቡን የሚመጥን ተፎካካሪ ፓርቲ አንዲኖርም ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን ነው የተናገሩት። ወንድወሰን ተሾመ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ/ኢዴፓሐ ስራ አፈፃሚ አባልና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ “ኢትዮጵያ ከሰባ በመቶ በላይ የዚህ አገር ፖለቲካ ባለቤት መሆን ያለበት ይሄ ወጣት ነው “ ብለዋል፡፡  አቶ ተሻለ ሰብሮ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ/ኢራፓ /ፕሬዝዳንት በብሄራዊ መግባባትና እርቀ ሰላም በመደጋገፍ ከሚሰሩ የኢትዮጵያ ተራማጅ ደጋፊዎችና ተባባሪዎች ጋር ሪፎርሙን በአዲስ አመት እንዲጠናከር እንዲሚሰሩም ተናግረዋል፡፡  ፓርቲዎቹ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልክት ያስተላለፉ ሲሆን አዲሱ ዓመት አሁን የተጀመረውን ሁለንተናዊ ለውጥ ዘላቂ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም