በክልሉ ለተጀመረው የህግ ማስከበር ሥራ ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ

86

ባህር ዳር፤ ግንቦት 15/2014 (ኢዜአ)፡ በአማራ ክልል ህዝቡን እረፍት ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ስርዓት ለማስያዝ ለተጀመረው ህግ የማስከበር ሥራ ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲያጠናክር የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።

 በክልሉ ህግን ለማስከበር በተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አስታውቋል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  ''በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከአሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ ተቀብለው ክልሉን የብጥብጥና የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው'' ብለዋል።

ባለፈው አንድ ሳምንት በአማራ ክልል በተጀመረው ህግ የማስከበር ሥራ 4 ሺህ 552 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከልም 210 በነፍስ ግድያ ተጠርጥረው የሚፈለጉ ግለሰቦች ሲሆኑ 40ዎቹ ደግሞ ቀደም ሲል ተፈርዶባቸው በተለያየ ምክንያት ከማረሚያ ቤት ያመለጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

እንዲሁም  ከ917 የሚበልጡ ጸጉረ ልውጦች ''ከውስጥ ባንዳ ጋር በማበር ክልሉን ለማተራመስ ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ናቸው'' ብለዋል።

የተሰጣቸውን ህዝባዊ ሃላፊነት ባለመወጣት በልዩ ልዩ ወንጀሎች ተሳትፈው የተገኙ ከ1 ሺህ 780 በላይ የፀጥታ አካላትም በቁጥጥር ስር እንደዋሉ አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል።

ሌሎቹ ደግሞ ከልሉን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ በቡድንና በግል ሲንቀሳቀሱ በክትትል የተደረሰባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።

የክልሉን ህዝብ እረፍት ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን ስርዓት ለማስያዝ እየተካሄደ ላለው ህግ የማስከበር ስራ ህዝቡ ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን እያደረገ ላለው ድጋፍና ትብብርም ኃላፊው አመስግነዋል።

የተጀመረው ህግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ደሳለኝ፣ የክልሉ ህዝብ በህግ ማስከበር እንቅስቃሴው ለመንግስት እያደረገ ያለውን ድጋፍና ትብብር  አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም