በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሶስት ወራት ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች በባህላዊ ፍርድ ቤቶች እልባት እንዲያገኙ ተደርጓል

ግንቦት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ)በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ በሶስት ወራት ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ የክስ መዝገቦች በባህላዊ ፍርድ ቤቶች እልባት እንዲያገኙ መደረጉ ተገለጸ።

ፍርድ ቤቶቹ ባህልና ወግን በጠበቀ መንገድ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በእርቅ እየፈቱ እንደሆነ ተነግሯል።

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በሶስት ወራት ውስጥ የተቋቋሙ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አፈጻጸም የተመለከተ ውይይት በጭሮ ከተማ ተካሄዷል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቡካር ከዲሮ በዞኑ በሶስት ወራት ውስጥ ከቀረቡት 2 ሺህ 954 መዝገቦች 2 ሺህ 230 ጉዳዮች በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ማግኘታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ፍርድ ቤቶቹ የሚጠቀሙት የመደበኛ ፍርድ ቤቶች ሕግን ሳይሆን ባህላዊ ሕጎችን ነው ብለዋል።

በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የቀረቡ ጉዳዮች በባለ ጉዳዮቹ ፈቃደኝነት ላይ በመመስረት ጉዳዩ በባህላዊ ፍርድ ቤት እንደሚታይ አመልክተዋል።

ፍርድ ቤቶቹ ባህልና ወግን በጠበቀ መንገድ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በእርቅ እየፈቱ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ በገጠራማ አካባቢ የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የስራ ጊዜያቸውንና ለመጓጓዣ የሚያወጡትን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶላቸዋል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ ወይዘሮ አዱኛ አህመድ በበኩላቸው በባህላዊ ፍርድ ቤቶች አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች በግልጽና በእውነተኛ መንገድ ፍትሕን የማስከበር ስራቸውን በተጠናከረ መልኩ ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ተተኪው ትውልድ ባህል ወግና ስርዓት የሚያከብር እርስ በእርሱ የሚዋደድ የሚደማመጥ እንዲሆን ባህልን የማስተማሪያ መድረኮችንም ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ እንደሚፈጥሩ አመላካች ተስፋ አለ ብለዋል።

አባገዳ ሻሚል አህመዶ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህን መሬት የማስያዝ ስራ እየሰሩ እንደሆነና እርቅን መሰረት ያደረገ የፍትህ አሰጣጥ ዘዴን የሚከተሉ በመሆኑ የውሸት ማስረጃንም በማስቀረቱ በኩል ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ እንደሆነ አመልክተዋል።

ባህልን አስጠብቆ የግጭት አፈታት ስርዓትን በመዘርጋት ለመጪው ትውልድ የማስረከብ እንዲሁም ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የተከባብሮ የመኖር እሴት ማሳያ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ጨፌ ኦሮሚያ በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብስባ በኦሮሚያ ክልል ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 240/2013 ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ጫና ከማቀለል አኳያ ያላቸው ፋይዳ ወሳኝ እንደሆነም ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም