የበግ ገበያው የተሻለ ዋጋና አቅርቦት የታየበት መሆኑን ሸማቾች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የበግ ገበያው የተሻለ ዋጋና አቅርቦት የታየበት መሆኑን ሸማቾች ተናገሩ
ጳጉሜ 3/2010 በአዲስ አበባ የዓዲስ ዓመት የበግ ገበያ አቅርቦትና ዋጋ ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው ሸማቾች ተናገሩ፡፡ ዘንድሮ የተፈጠረው ሰላማዊ እንቅስቃሴ የበግ ገበያ ደመቅ እንዲል አድርጎታል ሲሉም ነው ሸማቾቹ የጠቀሱት፡፡ ከነዋሪዎች መካከል በዊንጌት የበግ ገበያ አካባቢ በግ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ ሙሉሰው ታደለ እንደጠቆሙት ባለፈው ዓመት እስከ አራት ሺህ ብር ይሸጥ የነበረው የበግ ዋጋ በዘንድሮ ዓመት እስከ ሁለት ሺህ ብር እየተገዛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የዋጋ መውረድ የተፈጠረው በግ በብዛት ወደ ገበያ በመቅረቡ መሆኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ገበያ ያገኘናቸው አቶ ታዬ መርጊያ ባለፈው ዓመት በነበረው አለመረጋጋት ጥሩ በግ ሊገዙ እንዳልቻሉ ገልፀው ዘንድሮ የሚታየው ሰላማዊ እንቅስቃሴ በዓሉን ድርብ እንዳደረገላቸውና የተሻለ በግ በሁለት ሺህ ስምንት መቶ ብር እንደገዙ ጠቁመዋል፡፡ ሌላው ቀጨኔ በግ ተራ ያገኘናቸው አቶ በርሱፍቃድ አየለ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ የበግ አቅርቦቱ በበቂ ሁኔታ ወደ ማእከላት ባለመግባቱ የበግ ዋጋ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው አሁን በተመጣጣኝ ዋጋ ሊገዙ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ በዊንጌት ገበያ በግ ሲሸጡ ያገኘናቸው አቶ በዴቻ በቀለ በበኩሉ በጎችን ከሰንዳፋ በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው እንደመጡና ገበያው ጥሩ መሆኑን ጠቁሞ ባለፈው ዓመት በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ወደ ከተማ አለመምጣታቸውን ጠቁሟል፡፡ በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የግብይት ክትትል ተሳታፊዎች ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን በቀለ በበኩላቸው ዘንድሮ በግና ፍየልን ጨምሮ የቁም እንስሳት አቅርቦት ካለፉት ዓመታት በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩን ተናግረዋል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ ወደ ከተማዋ ከሁለት ሚሊዮን ያልበለጠ የቁም እንስሳት ወደ ገበያ ገብቶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ ችግር በመፈታቱ እስከ ስድስት ሚሊዮን የቁም እንስሳት ከሁሉም አካባቢዎች በስፋት ወደ ገበያ መግባቱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቁም እንስሳት ገበያ ማእከል በአንድ ቀንድ ከብት አስር ብር በበግና ፍየል ደግሞ አንድ ብር በመሰብሰብ አስተዳደሩ በርካታ ገቢ እያገኘ እንደሆነ ተናግረው የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል የክፍያ ገቢውንም የማሻሻል ስራ እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡