"እኛው በኛው ብንረዳዳ ጎዳና ላይ ልጆች አናይም" - ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ

407

ሀዋሳ ግንቦት 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያዊያን እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል እየጎለበተ መምጣቱን የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ተናገሩ ፡፡

በሀዋሳ “ለአረጋዊያን ክብር እንጓዛለን” በሚል መሪ ሀሳብ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ዕውቅ አርቲስቶች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት የእግር ጉዞ ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ከተመሰረተ 29ኛ ዓመቱን የያዘው ድርጅቱ ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋዊያንን በመንከባከብና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ደግፎና አስተምሮ ለቁምነገር ለማብቃት መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡

በተለይ ላለፉት 17 ዓመታት "ኢትዮጵያዊያን ለኢትዮጵያዊያን" በሚል መርህ በሀገር ልጆች ሀብት ላይ ተመስርቶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በአሁኑ ወቅት እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህላችን እየጎለበተ መጥቷል ብለዋል፡፡

የእግር ጉዞው አላማ አረጋዊያን ሊያገኙ ስለሚገባቸው ፍቅርና እንክብካቤ ግንዛቤ ማስጨበጥና ገቢ ማሰባሰብ እንደሆነም ሲስተር ዘቢደር ገልጸዋል፡፡

በተለይ በኑሮ ውድነት ምክንያት በርካታ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው አረጋዊያን ለችግር ስለተጋለጡ ከጎረቤቶቻችን ጀምረን የተቸገሩ ወገኖቻችንን መጎብኘትና ማገዝ ይጠበቅብናል ብለዋል ፡፡

በእግር ጉዞው መርሃ ግብር ላይ ከተገኙት መካከል አርቲስት ይገረም ደጀኔ በበኩሉ የመደጋገፍ ባህላችንን ከዚህ በላይ እያጠናከርን ዛሬ ላይ አቅም ያጡትን ልንደርስላቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ እርስ በርስ የመደጋገፍ እሳቤ እንደ ሀገር የምንመለከታቸውን አስከፊ ነገሮች በማስወገድ መልካም ገፅታ እንድንገነባ የጎላ አስተዋፅዖ የሚያበረክት ነውም ብሏል ፡፡

ሌላዋ ተሳታፊ ዶክተር ሳሮን ሀብቶም በበኩሏ "አረጋዊነት ሁላችንም ከፊታችን የሚጠበቅብን ፀጋ ነው" ብላለች ፡፡

መስራትና መደገፍ በምንችልበት በወጣትነት ዕድሜያችን አረጋዊያንን መንከባከብና መደገፍ ነገ የሚደግፉንን ተተኪዎች ማፍራት ያስችለናል ያለችው ዶክተር ሳሮን ለዚህ በጎ ተግባር ይበልጥ መነሳሳት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች፡፡

የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደግፌ ዳንኤል ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሀዋሳ ከተማ በርካታ ጧሪ የሌላቸውን አረጋዊያን ከወደቁበት በማንሳት እፎይታን እያስገኘላቸው የቆየ ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

የከተማው ባለሃብቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች "አረጋዊያንን የመደገፍ ግንዛቤያቸው እየጨመረ ነው" ያሉት አቶ ደግፌ፤ ከተማ አስተዳደሩ ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን ታዳሚዎች በአጭር የገቢ ማሰባሰቢያ የስልክ መልዕክት ኮድ 9600 ለሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ገንዘብ ገቢ አድርገዋል፡፡

ድርጅቱ በሀዋሳ ከተማ ባቋቋመው ሁለገብ የአረጋዊያን ማዕከል ውስጥ 120 አረጋዊያንን፣ ቤት ለቤት በሚሰጠው የድጋፍ አገልግሎት ደግሞ 150 አረጋዊያን እንዲሁም 100 ሕፃናትን እየረዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም