የህዝብ ብሶትና መራር ትግል የወለደው ለውጥ እና የለውጡ አደናቃፊዎች አገር የማፍረስ ጥረት ከየት እስከየት?

ግንቦት 14/2014/ኢዜአ/ የህዝብ ብሶትና መራር ትግል የወለደው ለውጥ እና የለውጡ አደናቃፊዎች አገር የማፍረስ ጥረት ከየት እስከየት?

ኢትዮጵያውያን ለአብሮነትና ለወንድማማችነት ክብር የሚሰጡና ለአገር ሕልውናም አብረው የሚሰዉ ሕዝቦች መሆናቸው የትናንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዛሬም እውነት ነው።

ነገር ግን በጥላቻ በሰከሩ ኃይሎች የተሞላው አሸባሪው ህወሓት ይህንን እውነት ለመናድ ቀን ከለሊት መስራት የጀመረው ገና ከምስረታው ጀምሮ ነበር።

ለከፋፋይ ሴራው ስኬት አማራጭ ያደረገው ደግሞ ደስታንም፣ ሀዘንንም እኩል ተጋሪ የሆኑ ወንድማማች ህዝቦች በጠላትነት የሚተያዩባቸውን ትርክቶች መርጨትን ነው።

በዚህ መንገድ አልሳካለት ሲለው በሀሳብ የሞገቱትን የራሱን አባላት ሳይቀር በመረሸን፤ ንጹሀንን በመግደል፣ በመሰወር፣ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን በመፈጸም በኃይል ፍላጎቱን ለማሳካት ሲሰራ ቆይቷል።

የህወሓት ግፍና በደል ያንገሸገሻቸው ኢትዮጵያዊያን ህወሃት መራሹን መንግስት እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ መለወጥ የቻሉ ሲሆን፤ የለውጡ ሂደት ግን አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡

ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ውጤቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም በዚሁ ልክ የተለያዩ ፈተናዎችም አልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱት ከ100 በላይ ግጭቶች ዋና አስፈፃሚው አሸባሪው ህወሃት መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች መገለጹ ይታወሳል።

"እኔ የማልመራት ኢትዮጵያ ትፍረስ" ብሎ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት የሚያሴራቸው የጥፋት ወጥመዶች ብዙዎቹ በጸጥታ ሃይሉና በህዝቡ ጥረት ቢከሽፉም  ጥቂት የማይባሉት ግን የሰለማዊ ዜጎችን ህይወት ከመቅጠፍ ጀምሮ በሃብት ንብረት ላይ ውድመት አድርሰዋል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ደግሞ አፈናቅለዋል፡፡

ለአብነትም በጌዲዮ፣ ቡራዩ፣ ሀዋሳ፣ መተከል፣ አጣዬ፣ ድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ ኮንሶና በሌሎች አካባቢዎችም ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ብዙ ጥፋት አድርሰዋል፡፡

በወቅቱ ኢዜአ ግጭት ተከስቶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ያነጋገራቸው ወገኖች የችግሩ ሁሉ መንስኤ ጥቅማቸው የተነካባቸው የግጭት ነጋዴዎች እንጂ  በህዝብ ዘንድ ምንም አይነት ጥላቻ እና ቂም እንደሌለ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ግጭት ተከስቶባቸው ከነበሩ ከተማዎች መካከል የሻሸመኔ ከተማ አንዷ ስትሆን፤ የከተማዋ  ከንቲባ ወሾ ከድር ሻሸመኔ ከየትኛውም አካባቢ መጥተው በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት እንጂ ለጥል እና ግጭት ምክንያት የሚሆን አንዳችም ነገር እንዳልነበር ያስረዳሉ።

የጥፋቱ ምክንያት ለውጡ መጣብን ብለው ባኮረፉ ሃይሎች ተጠንስሶ የማያባራ ግጭት ለማስከተል የተሸረበ ሴራ እንደነበረም ነው ያስታወሱት።

የሻሻመኔ የጥፋት ተላላኪዎች ሴራ ከከሸፈ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከተማዋ በሕዝቡ ትብብር ዳግም ተገንብታ የወትሮው ሰላምና አብሮነት መቀጠሉን ገልጸዋል።

ትልቁ ነገር የሴረኞች መጠቀሚያ አለመሆንና የአካባቢን ሰላምና ጸጥታ በመጠበቅ ረገድ ባለቤት ሆኖ መገኘት መሆኑን ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሺዮሎጂ መምህር ዶክተር ወልድአብ ተሾመ፤ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት በዘመናት የጉዞ ሂደት የማሕበራዊ ትስስር እንዲላላ እና የጋራ እሴቶች እንዲሸረሸሩ በመሰራቱ መሆኑን ይናገራሉ።

"ጠንካራ ማሕበራዊ ትስስር የሌለው ማህበረሰብ ማገር እንደሌለው ቤት ይቆጠራል" የሚሉት መምህሩ፤ ከምንም አስቀድሞ የጋራ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ማጠናከር ላይ መስራት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡

ከግጭቶቹ ጀርባ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ስውር እጆች ተሳትፎ እንደነበረበት ገልጸው፤ የጥፋት ሃይሎች ፍፁም መዳረሻ እንዳይኖራቸው ለማስቻል አገራዊ እሴቶችን ማጠናከር ላይ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው ለውጡ በሚራመድበት ፍጥነት ልክ መጓዝ ካቃታቸውና ለውጡን ለማሰናከል  የጥፋት መንገድ ከተከተሉ ሃይሎች ዋነኛው አሸባሪው ህወሓት መሆኑን ይናገራሉ።

በዚህም የአሸባሪው ሕወሓት መሪዎችና ተላላኪዎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፉት ሀብት መልሰው ኢትዮጵያውያንን ለማጋደል አውለውታል ብለዋል።

ሀሰተኛና የተጭበረበሩ መረጃዎችን በማምረትና እውነታዎችን በማባዛት ጭምር የግጭቶቹ ሁሉ መሪ ተዋንያን በመሆን መስራታቸውን ተናግረዋል።

ለሴረኞቹ ድርጊት አባባሽ ምክንያቶች መካከል ያልሰለጠነ የፖለቲካ ባህል፣ የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሳብ መንሰራፋት ታክሎበታል ሲሉ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያን ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ ተከትሎ እንድትፈርስ የሚሹ የውጭ ሃይሎችም የነበራቸው ተሳትፎ ቀላል አልነበረም ይላሉ ዶክተር ቢቂላ።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለሚደረገው ጥረት አሸባሪው ህወሃት "የአንበሳውን ድርሻ ይዞ" የጥፋት ሃይሎችን በማሰልጠን እና ስምሪት በመስጠት የነበረውን ጥረት አስረድተዋል።

እነዚህን ሁሉ የጥፋት እንቅስቃሴዎች በመመከት መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር የፈፀመውን ገድል አስታውሰው በዚህ ልክ ባይሰራ ኖሮ የሚደርሰው ጥፋትም በእጅጉ የከፋ እንደነበር ገልጸዋል።

በእነዚህ የጥፋት አጀንዳዎች ውስጥ በመሳተፍ የተያዙ ሰዎችን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት  ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ደግሞ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ጸጋ ይናገራሉ።

የወንጀል ተሳታፊ በሆኑ አካላት ላይ ተገቢው ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ በብዙዎቹ ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

የምርመራ ውጤቶቹ እንደሚያመለክቱት በተለያዩ አካባቢዎች ለተከሰቱት ግጭቶችና ለደረሰው ጥፋት ዋነኛው ተዋናይ አሸባሪው ህወሓት መሆኑንም ገልጸዋል።

የጥፋት ሃይሎች አገር የማፍረስ እንቅስቃሴ አሁንም የቀጠለ ቢሆንም መንግስት ችግሮችን እየተጋፈጠ በማለፍ የሚታይ ውጤት እያስመዘገበ መቀጠሉንም ነው ዶክተር ቢቂላ የሚናገሩት።

መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በማለም ሁሉን ያካተተ አገራዊ ምክክር ለማከናወን በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የህዝብ ብሶትና መራር ትግል የወለደው ለውጥ በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችና አገር ወዳዶች ትግል በብሩህ ተስፋ ታጅቦ የቀጠለ ሲሆን የለውጡን አደናቃፊዎች እኩይ አላማ ለመግታት መላው ህዝብ ከመንግስት ጎን እንዲቆምም ነው ዶክተር ቢቂላ ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም