በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊና የደህንነት ስጋቶችን በመተንተን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መዘጋጀታቸውን ተመራቂ መኮንኖች ገለጹ

134

ግንቦት 13/2014 (ኢዜአ) በአፍሪካ ቀንድ ወታደራዊና የደህንነት ስጋቶችን በመተንተን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መዘጋጀታቸውን የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ተመራቂ መኮንኖች ገለጹ።

የመከላከያ ዋር ኮሌጅ በደህንነትና ስትራቴጂ ጥናት ላይ ለአንድ ዓመት ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያና የጎረቤት አገራት ወታደራዊ መኮንኖችና ሌሎች የደህንነት አመራሮች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አህመድ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮችና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው መኮንኖች በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ ሀገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ የደህነንነትና ስትራቴጂክ ጉዳዮችን መተንተን እና የውሳኔ ሀሳብ ማመንጨት የሚያስችል እውቀት እንዳገኙ ተናግረዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የወታደራዊ ጉዳዮች አስተባባሪዋ ሜጀር ጀኔራል ጥሩዬ አሰፌ፤ ከተመራቂዎቹ መካከል አንዷ ሲሆኑ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም መኮንኖችን ወደ ውጭ አገር እየላከ ያስተምር እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የመከላከያ ዋር ኮሌጁ በመቋቋሙ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች መኮንኖች በአገር አቅም ለማስተማር መቻሉን ገልጸዋል።

በኮሌጁ በነበራቸው ቆይታ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ጉዳዮችን በመተንተን ስትራቴጂክ ጉዳዮችን ማቀድ የሚያስችል እውቀት ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

ሌላኛው ተመራቂ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ባለሙያው ይርጋ ባድማ፡ በስልጠናው በዘመኑ ልክ ብቁ ሆኖ ለመገኘት የሚያስችል ትምህርት እንዳገኙ ገልጸዋል።

በኮሌጁ የመጀመሪያ ዙር ሰልጥነው ከተመረቁት የጎረቤት አገራት መኮንኖች መካከል ደቡብ ሱዳናዊው ብርጋዴር ጀኔራል ማኪኒ ማኩር፤ የኢትዮጵያ መንግስት የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ መኮንኖች ጭምር የሚማሩበት የመከላከያ ዋር ኮሌጅ ማቋቋሙ ሊደነቅ ይገባዋል ብለዋል።

ኮሌጁ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምን ማስፈን የሚችሉ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም አድንቀዋል።

በትምህርት ቆይታቸው በአፍሪካ ቀንድ ተለዋዋጭ የሆኑ አለመረጋጋቶችን በአግባቡ በመተንተን ቁልፍ የደህንነት ስትራቴጂ መቀየስ የሚያስችል አቅም ማዳበራቸውን ገልጸዋል።

የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንትና የዋር ኮሌጁ ተመራቂ ሜጀር ጀኔራል ሀብታሙ ጥላሁን፡ "ወታደር ስልጠናን የህይወቱ አንድ አካል አድርጎ መውሰድ አለበት" ።

በዋር ኮሌጁ ያገኙት እውቀት ወታደራዊ አመራሩ አገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን መተንተን፤ ሰራዊቱን የሚመሩበትን ሁኔታ ማቀድ፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ተረድቶ ለሰራዊት ግንባታ ትኩረት በመስጠት ለአገር ደህንነት መጠበቅ በትኩረት እንዲሰራ ያስችላል ነው ያሉት።

የደቡብ ሱዳኑ ተመራቂ ብርጋዴር ጀኔራል ማኪኒ ማኩር  ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ሀገር ሆና እንድትቀጥል ከምስረታ ጀምሮ ከጎናቸው መቆሟን በማንሳት፤ በቀጣይም የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ወዳጅነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሚያጋጥማት ማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ደቡብ ሱዳን ከጎኗ ትቆማለች ሲሉም አረጋግጠዋል።

ተመራቂ መኮንኖች በቀጣይ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ትልቅ ሃላፊነት እንደሚጠብቃቸውም እንዲሁ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም