የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለአብርሆት ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፍት አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለአብርሆት ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፍት አበረከተ

ግንቦት 13/2014 (ኢዜአ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፍት አበረከተ።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲሱ ማሞ፤ ለበጎ አላማው ስኬት የድርሻችንን ለመወጣት መጽሃፍቱን አስረክበናል ብለዋል።
ለአብርሆት ቤተመጽሐፍት የተሰጡ መጽሐፍት በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት ለሚሳተፉ ወጣቶችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ጥሩ ግንዛቤ የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ብዙዎቹም በጅማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ ካለው አክሽን ጄል ከተባለ የውጭ ኩባንያ መሰብሰባቸውንም ገልጸዋል።

እነዚህን መጽሐፍት በዛሬው እለት ለአብርሆት ቤተ መጽሐፍት ኃላፊ አቶ መስፍን ገዛኸኝ አስረክበዋል።
የትውልዱን አእምሮ ለመገንባት እውን ለሆነው የአብርሆት ቤተ መጽሃፍት በቀጣይም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የአብርሆት ቤተ መጽሐፍት የንባብ አገልግሎትን በመስጠት የእውቀት ማእከል እንዲሁም የቱሪዝም ማእከል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን አቶ መስፍን ገልጸዋል።
ቤተ መጽሃፍቱ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለዓለም ተመራማሪዎች የሚያገለግል ትልቅ ሃብት መሆኑንም ጠቅሰዋል።