ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ዘርፍ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኘች


ሰመራ፤ ግንቦት 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።


ዘርፉ ለአጠቃላይ አገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 5 ነጥብ 2 በመቶ እንደሆነም ተገልጿል።


"ቱሪዝም ለስራ እድል ፈጠራ" በሚል መሪ ቃል 10ኛው ሀገር አቀፍ ጉባኤ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።


የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ500 ሺህ የአገር ውስጥና ውጪ ጎብኚዎች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።


በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በጦርነቱ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር መጨመርና አዳዲስ የቱሪዝም የገበያ እድሎችን ማመቻቸት ትኩረት እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።


የቱሪዝም ዘርፉ በአሁኑ ለአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት(ጂዲፒ) ያለው ድርሻ 5 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ ለማሳደግ እምቅ ሀብቶችን ማልማት ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።


የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነቢሃ መሀመድ የዓለም ጎብኚን ቀልብ የመሳብ እምቅ አቅም ያላቸው የቱሪዝም ሃብቶች አልምቶ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አኳያ ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ገልጸዋል።


በቱሪዝም መስክ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል ማፍራት፣መዳረሻዎች የማልማትና ማስተዋወቅ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት የቅንጅት አሰራር አለመጠናከር ከዘርፉ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ተናግረዋል።


የቱሪዝም ሀብት ለውጭ ምንዛሬና ለስራ እድል ፈጠራና በአግባቡ ማዋል ከተቻለ ዘርፉን የኢትዮጵያ ቁልፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር ማድረግ ይቻላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የግሉ ዘርፍ ያሳተፈ ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል።


የአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ አህመድ አብዱልቃድር በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ከ75ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መደረሻዎችን መጎብኘታቸውን ጠቁመዋል።


የክልሉን የቱሪዝም ሃብት ማስተዋወቅና መዳረሻዎች ማልማት፣ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የሚችል ብቁ የሰለጠነ ኃይል ማፍራት በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።


የቱሪዝም ዘርፉ የዜጎችን ሕይወት መቀየር ወደሚችል አቅም ለመቀየር ክልሉ በትብብር ከዘርፉ ባለድርሻዎች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


የሀገር አቀፍ ጉባኤው ተሳታፊዎች ነገ በአፋር ክልል የሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።


ቱሪዝም በዓለም ኢኮኖሚ የ10 ነጥብ 3 በመቶ ድርሻ እንዳለው የዓለም የጉዞና ቱሪዝም ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።


የጉዞና የቱሪዝም ዘርፍ እ.አ.አ በ2021 ለዓለም ኢኮኖሚ 5 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር ማመንጨቱ ተገልጿል።


ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ ‼️
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼️
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼️
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼️

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም