የፌደራል መስሪያ ቤት ሰራተኞች የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል ፍጻሜውን አገኘ

44

ግንቦት 13/2014 ( ኢዜአ) በባህልና ስፖርት ሚኒስትር አዘጋጅነት ከመጋቢት 15 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የፌደራል መስሪያ ቤት ሰራተኞች የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል ፍጻሜውን አግኝቷል።

በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው የስፖርት ለሁሉም ፌስቲቫል እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቅርጫት ኳስን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ፉክክር ተደርጎበታል።

በዚህ ውድድር በእግር ኳስ ወንዶችና በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ጾታ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።

በጠረጴዛ ቴንስ በሁለቱም ፆታ እና በቼስ የወንዶች ውድድር ኢትዮ- ቴሌኮም አሸናፊ ሆኗል።

በቮሊቮል የወንዶች ውድድር ፌደራል ማረሚያ ቤት፣ በሴቶች አንበሳ ከተማ አውቶቡስ የዋንጫ አሸናፊዎች ሆነዋል።

በሌሎች የተለያዩ ስፖርቶች ሲደረጉ የነበሩ ውድድሮች አሸናፊዎቹ ተለይተው የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቶቸዋል።

በውድድሩ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።

ጤናማ ሰራተኛ ለመፍጠር ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምዱ እንዲያድግ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍና እገዛ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

እንዲዚህ አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከርና እንደ ሀገር እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አጋዥ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሰራተኞች የስፖርት ለሁሉም ፊስቲቫልና በቀጣይ ዓመት በተጠናከረ መልኩ እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት።

በውድድሩ  ከ30 በላይ የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተካፈሉ ሲሆን የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ  ቡድኖች በሀገር አቀፍ ደረጃ በደሴ ከተማ በሚደረገው ውድድር ተካፋይ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም