ሽምግልና በሚፈልጉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሽምግልና ስራዎችን እየሰራን ነው

242

ጅማ፤ ገንቦት 12/2014 (ኢዜአ) ሽምግልና በሚፈልጉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሽምግልና ስራዎችን በመስራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የየጅማ ከተማ አካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

 የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ወጣቱን በመምከርና በመገሰጽ እንዲሁም የተጋጩ አካላትን በማስታረቅ ለአካባቢ ሰላም የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም  የፀረ ሰላም ቡድኖች ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት ሙከራዎች እየከሸፉ መምጣታቸውን አመልክተዋል።

አባ ገዳ ሼህ ነኢም አባ መጫ እንዳሉት በጅማ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎችና የሀይማኖት አባቶች  በአካባቢ የሰላም ጉዳይ ላይ በትብብር እየሰሩ ነው።

በጅማ ከተማና በአካባቢው የሰላም ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ ስራዎችን እየሰሩ እንደሆነ የገለጹት አባገዳ ሼህ ነኢም "አሁንም የሀገር ሽግሌዎች የሚጠበቅብንን እያደረግን ነው" ብለዋል፡፡

በዚህም በአካባቢው የተፈጠሩ ችግሮችን በማረጋጋት በርካታ ግጭቶን ፈተናል፣ ጥፋቶችን አስቀርተናል፣ ያኮረፉ አካላትን በማስታረቅ ሰላም መፍጠር ችለናል ብለዋል፡፡

ሽምግልና በሚፈልጉ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የሽምግልና ስራዎችን በመስራት ሃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የባህላዊ ዳኝነት ቦታ ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን ያመለከቱት አባገዳ ሼህ ነኢም፤ የትኛውም አካባቢያዊ ጉዳዮች በሽምግልና ታይተው መፍትሄ እንዲሰጣቸው እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በሀገር ባህል የሽምግልና ልምድ መሰረት ሁሉም ለሽማግሌ መታዘዝ፣ የታላላቆችን ምክር መስማት የቆዩ እሴቶች በመሆናቸው ይህንኑን ለማስቀጠል እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሀገር ሽማግሌና የጅማ የሃይማኖት አባቶች ጉባኤ ሃላፊ ሀጂ ቢያ አባ መጫ በበኩላቸው "እኛ የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢው በፀረ ሰላም ሃይሎች ሊፈጠሩ የነበሩ በርካታ ሙከራዎችን በጋራ ሆነን በመስራታችን ማስቀረት ችለናል" ብለዋል፡፡

በቅርቡ በሃይማኖት ሽፋን ግጭት ለመፍጠርና ጥፋት ለማድረስ የሞከሩ  አካላትን በማረጋጋት ጉዳዩን ለማብረድ ያደረጉት ጥረት ውጤት ማስገኘቱን አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ጸረ ሰላም ሃይሎች ሁከት በመፍጠር ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት ጥረት ቢያደርጉም በጋራ በተሰራው ስራ እኩይ አጀንዳቸውን ማፍረስ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ችግሮችንና አለመግባባቶችን በምክርና በውይይት ለመፍታት ከአካባቢው አስተዳደር ጋር  እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

"በፀረ ሰላም ቡድኖች የሚፈጠሩ አጀንዳዎችን በመቀበል የሚንቀሳቀሱ ወጣቶችን በመምከርና በማረጋጋት ቀንና ሌሊት በሰራነው ስራ በሽምግልና ስራችን ጥፋትን አስቀርተናል" ብለዋል፡፡

"የሽምግልና ስራችን ከሰላም ጋር የተያያዙ ችግሮችን መርምሮ በመፍታት የሚያቀራርቡ ሀሳቦችን በማፍለቅ የሚሰራ በመሆኑ አጠናከረን በመቀጠል ሰላማችንን እናስጠብቃለን።" ብለዋል።

ሽምግልና የተቆጣና የተናደደን አካል ለማረጋጋትና ከጊዜያዊ ስሜቱ ለመመለስ ትልቅ ሃላፊነትን የሚፈልግ በመሆኑ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ቢሰራበት ውጤታማ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም