ቀጥታ፡

የአርበኞች ግንቦት ሰባት አመራሮች አዲስ አበባ ገቡ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 4/2010 የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለመፎካከር ሳይሆን አገርን ለማረጋጋት መሆኑን ተናገሩ፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ዶክተር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሚመራው ልዑክ አዲስ አበባ ሲገባ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳውና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ዶክተር ብርሃኑ ከሁሉም በፊት ሰላማዊ ፖለቲካ ስለሚቀድም አገርን የማረጋጋት ስራ እንሰራለን ብለዋል፡፡ በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመዘዋወር ውይይት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ "በአገሪቱ ትርጉም ያለው ዲሞክራሲ ለመፍጠር ውይይትና ንግግር ያስፈልጋል" ያሉት ዶክተር ብርሃኑ አገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚቀርበው ሐሳብ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ብለዋል። ወደ ኢትዮጵያ የመጣነው ከመንግስት ጋር ለመወያየት ብቻ ሳይሆን በለውጥ ላይ ያለው የመንግሰት ኃይል አገሪቱን እንዴት መምራት አለበት በሚለው ላይ ለመነጋገር ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በዜግነት ላይ እንዲሆን አንፈልጋለን ያሉት ዶክተር ብርሃኑ ሁላችንም ያለን አንድ አገር ስለሆነ በጋራ ወደ ተረጋጋ ዲሞክራሲ መውሰድ አለብን ሲሉም ተናግረዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም